በወቅታዊ ጉዳይ”ከዐማራ ፋኖ በጎንደር” የተሰጠ መግለጫ

“…የዐማራ ሕዝብ የገጠመውን መንግሥት መር የኅልውና አደጋ ለመቀልበስ ዱር ቤቴ፣ አራዊት ዘመዴ ካለ ዓመታት ተቆጥረዋል። በየቀጠናው ነጻነትን ሽቶ፣ ግፍን ተጸይፎ፣ ኅልውናውን አስቦ በሐቅ ላይ መሠረቱን አድርጎ የፈነነው አርበኛ ተቋማትን እያሳደገ ወደ አንድ ማዕከላዊ ተቋም ማምጣት አስፈላጊነቱ ውሎ ያደረ ሐቅ ነው። ይህንን ጉዳይ በወጉ የተረዱ የዐማራ ሕዝብ የኅልውና ታጋዮች አንድ ድርጅታዊ አታጋይ ተቋም ለማቆም በብርቱ ከሚደክሙ ቀጠናዊ ተቋማት መካከል “የአማራ ፋኖ በጎንደር” አንዱ ነው።

“…እንደ ተቋም አንድ ዐማራዊ ድርጅት እንዲፈጠር ያለን ጽኑ ፍላጎት ከንግግር ባለፈ በተግባርም ጭምር ዋጋ የከፈልንለተና የምንከፍልለት መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ዳሩ ግን ተቋምን የምናዋልደው ለሕዝባችን ዘለቄታዊ ኅልውናን በማረጋገጥ ሂደት የጀመርነውን ትግል አንድ እርምጃ ወደፊት እንዲያስፈነጥር እንጅ ግለሰባዊ ክብርና ዝናን እንዲሁም መርኅ አልባ የሥልጣን ፍትወትን ለማስተናገድ እንዳልሆነ መላው ሕዝባችንና አርበኛው የሚገነዘበው ሐቅ ነው። መሠረታዊ ጉዳዩ ይህ ሆኖ እያለ “የዐማራ ፋኖ በጎንደር” አንድ ማዕከላዊ ድርጅት አዋልደናል በሚለው ውሳኔ ላይ እንደ ተቋም እንደሌለንበት ለሕዝባችንና ለመላው የትግል ጓዳችን ማስገንዘብ እንወዳለን።

“…ይሁን እንጅ ተቋማችን አንድ ዐማራዊ አታጋይ ድርጅት እንዲፈጠር ከሌሎች ጠቅላይ ግዛቶች ጋር የሚሠራ አመቻች ኮሚቴ መርጦ በመላክ በመርኅና በአሠራር የሚወለድ ተቋም እንዲፈጠር ብንሰይምም ከጅምሩ የአካሄድና የመርኅ ጥሰቶች ጭምር እንደነበሩበት በመሪያችን በኩል የይስተካከል አቋማችንን ብናሳይም ጉዳዩ ትኩረት ሳይሰጠው አድሮ እዚህ ደረጀ ደርሷል። ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ በተለያዩ ግለሰቦች ጭምር በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚቀርቡ ጉዳዮች ተቋማዊ አሠራርንና መርኅን ከመጣሳቸው ባሻገር የተቋማችንን እንዲሁም የሚዲያና የሕዝብ ግንኙነት መምሪያውን ይሁንታ ያላገኙ መሆናቸውን ለመግለጽ እንወዳለን።

“…በጥቅሉ ሕባችንም መሬት ላይ የሚገኘው አርበኛም የሚፈልጉት በሐቀኛ ዓላማ፣ መርኅና መታገያ ጉዳይ ተቃኝቶ ለወንድማዊና ጓዳዊ አንድነት በርትቶ የሚሠራ ሕዝባችን ለገጠመው የኅልውና ጥያቄ ዘለቄታዊ መፍትሔ የሚሰጥ፣ በሕዝቡም በታጋዩም ዘንድ ቅቡልነት ያለውን ተቋምና ሐቀኛ መሪዎችን በመፍጠር ሂደት ውስጥ ሁሉም ወገን በስክነት ለውይይትና ለአንድነት እንዲተጋ ተቋማዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

“ኅልውናችን በተባበረ ክንዳችን”
የዐማራ ፋኖ በጎንደር
ቀን ሐምሌ 12/2016 ዓ.ም

2 thoughts on “በወቅታዊ ጉዳይ”ከዐማራ ፋኖ በጎንደር” የተሰጠ መግለጫ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *