ሐምሌ ፬ ቀን ፳፳፲፮ ዓ/ም
የውይይት መነሻ
ትዝብትና ምክራዊ መልእክት ቁጥር ፩
የአማራ ህዝብና የኢትዮጵያ ችግር ውስብስብ ነው። ይሄው ለሃምሳ አመታት እንዳየነው ሁሉም የኢትዮጵያን ችግር በራሱ እና በራሱ መንገድ እፈታለሁ ብሎ ትግል እየጀመረ መጨረሻ ለራሳቸውም ውርደት ሽንፈትን የታሪክ አተላ ሆኖ ነው የቀረው። ኢትዮጵያም አሁን የምትገኝበት የመገራ አውድ ፈጥረው ተከታዪን ትውልድ በደም ውስጥ አቁመውት፥ አገሪቷን አዳክመው ተገኙ። ስለዚህ እኔ ቤተ መንግሥት ብገባ የኢትዮጵያ ችግር እፈታለሁ እኔም ንጉሠ ነገሥት ተብዬ እመለካለሁ የሚል ከአለ አንደኛ ወይ እንደ አብይ አህመድ አቅሙን ሳያውቅ ራሱን በራሱ አንቱ ያለ ነው ወይንም ዘገምተኛ አይምሮ ያለው ነው። እንደውም ሁላችንም ተባብረንም ተደምረንም የሀገርና የውጪ አማካሪ ቀጥረንም የኢትዮጵያን 5% ችግር መፍታት ከቻልን ታሪክ ያስታውሰናል ያከብረንም ይሆናል።
እንዲህ አይነት ተሰጥኦ ያለው ሰው በፋኖም በኢትዮጵያም ቢኖር ኖሮ ኢትዮጵያውያን በተለይ አማራው ለ50 አመታት እየታረደ እየተፈናቀለ እየተሰደደ አይኖርም ነበር። የግሪክ ፈላስፋ እንዳለው “አንዱ ትልቁ ዕውቀት አለማወቄን ማወቅ ነው” ብሏል። የሰው ልጅ ጥበብ እርሱ ራሱን በራሱ መዝኖ ማወቁ ነውን እባካችሁ እኔ ሊቀመንበር ብሆን በዩ ቲዩብ አንቱ እባላለሁ እሞገሳለሁ ከዛ ሚኒሊክ ቤተመንግስት እገባለሁ ብሎ የሚያስብ ካለ ፋኖን እዚሁ በትኖ እርሱም በህይወት ከቆየ ከጫካ ሳይወጣ እንደነ ካቢላ ለ40 ዓመት ታጋይ ሆኖ ያረጃል።
የፋኖ መሪ ለመሆን ራሳችሁን የምትመርጡ ሰዎች ማወቅ የሚገባችሁ ቁም ነገር
የፋኖ መሪዎች ነን የምትሉ አንድ ነገር የረሳችሁ ይመስለናል። አንደኛ ፋኖ የፖለቲካ ድርጅት አይደለም። ፋኖ እንደ ቻይና፣ እንደ ኢህአፓ፣ እንደ ሻቢያ፣ እንደ ሕወሃት የተወሰኑ ሰባት ወይንም 11 ሰዎች ተሰብስበው ፕሮግራም ጽፈው፣ ሀሳባቸውን ሸጠው፣ ከዛ በማርክስ፣ በኤንግልስና በሌኒን አጥምቀው ደቀ መዝሙር አድርገው በድርጅታዊ መዋቅር ጠርንፈው የያዙት አይደለም። ፋኖ እርሱንም ወገኑን ልብ መከላከል በፈቃደኝነት ከሰፈር ወደ መንደር፣ ከመንደር ወደ ወረዳ፣ ከወረዳ ወደ አውራጃና ክፍል ሀገር በፈቃደኝነት የተሰበሰበ ኃይል ነው። ዓላማውና ወንድማማችነት እንጂ የታሰረበት ሰንሰለት የለም። አልመስል ያለው ቀን፣ ሆዱ የሻከረ ቀን፣ አመራሩ በሚጠብቀው አቅም ልክ ካላሳተፈው ካልሰማው እንደ እኩል ካላየው ጠመንጃውን ይዞ ወደ ቤቱ እንዳይገባ የሚያደርገው ምንም አይነት ምድራዊ ኃይል የለም።
ስለዚህ ከላይ ሆኞ ሊቀመንበር ብባል አዛዥ ናዛዥ እሆናለሁ ብላችሁ የምታስብ ሰዎች ካላችሁ ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ትሰራላችሁ። ፋኖ ሳምንት ሳይሞላ መፍረካከስ ላይ ይገባል። ስለዚህ ይህ በኢትዮ360 ሚዲያ ወይንም በሌሎች የዲያስፓራ ዩቲ ዩቦች ለሳምንት ጀግና ጀግና ታላቁ ቆራጡ ያስብላል ይሆናል። ይህ ግን ከታች በፈቃዱ የተሰባሰበውን ኃይል ልብ ካልገዛ የፋኖ ግንባር ተብሎ ተደብቆ ፀሀይ ሲወጣ እንደ ጤዛ የረገፈውን ማስታወስ በቂ ነው።
አሁንም የሚመረጠው አቶ እከሌ አንቱ በተባለ በሳምንቱ ተንከራታች ነው የሚሆነው። ይህ ጥንቆላ አይደለም የፋኖን ልዩ ባህርይ ከመረዳት የመጣ ነው። ፋኖ ኢህአፓ፣ ሕወሃት፣ ሻቢያ፣ ቀዩ ጦር፣ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የጠረነፈው ድርጅት አይደለም። ፋኖ በወገን እልቂት እና በአገር ስስት፥ በፍቅርና በወንድማማችነት ስሜት የተሰባሰበ ኃይል ነው። መሪዎቹም እንደዚሁ “እኔ” ያማይሉ በፍቅርና በሕዝብ ስስት ለሌላ የሞኖር መሆኑ ግንድ ይሆናል። ካልሆነ ፋኖዎች በእሤት፥ በትግል ግብና ርእዮት የማይመስላቸው፥ በደማቸው ላይ መንገሥ የሚሻውን መሪ አይቀበሉትም።
ለዚህ ምን አይነት አመራር ያስፈልገዋል ቢባል ለራሱ አንቱ ለመባል የሚጋፋ ሳይሆን ከዚህ በፊት ፋኖዎች ከሁሉም ክፍለ ሀገር ተሰባስበው እንደመሠረቱት እይን ከግለሰብ በላይ የሆነ ምክር ቤት ነው። ይህ የሁሉንም ኃይል ባለው የሠራዊት ቁጥር መቀመጫና ውክልና ያለው፣ ሁሉም ሀሳቡን የሚሰጥበት፣ ሰብሳቢው አዛዥ ሳይሆን አወያይና (Consensus builder)/ሆኖ ሁሉም እኔ የተነሳሁበት አላማ ግብ ለማድረስ በዚህ መቆየት አለብኝ የሚል መሆን አለበት። ሰብሰባዊ በምክር ቤቱ ውክልና ከሌላ ሶስተኛ ወገን ጋር ለመነጋገር የሚወከል እንጂ አንደ ኮሚስት መሪ ፈላጭ ቆራጭ አይሆንም። የግል ዝናውንም እየናኘ የህዝብን አቅምና ዋጋ ለግሉ ተክለ ሰውነት መገንቢያ አያደርገዉም። ሁሉም ፋኖዎች እኩል ክብር አላቸው፥ ነፍሳቸውን ለሕዝባቸውን ለአገራቸው ለመስጠጥ የወጡ እንጂ ግለሰቦችን ለማንገሥ የተገዙ ቅጥረኞች አይነደሉም።
ወንድሞች እንዳትሳሳቱ ዛሬ አቶ ገሌ ሊቀመንበር አቶ እገሌ ደግሞ ጸሀፊ ተደረገ ማለት ሌሎቹ ይታዘዙታል ማለት አይደለም። የልብ ለልብ ወንድማማችነት ከሌለ፥ ግልጸኝነትና የሞራል ልዕልና ካልመራ፥ ከልሰዋላችሁ ወደ ተሰዉልኝ የሚረማመድ ግለሰብ መሪ ከሆነ ራሱን ለሕዝቡ የሰጠው አጠቃላይ ፋኖ እንደተሸጠና መጠቀሚያ እንደሆነ ይሰማዋል፤ ያን ግዜ መሪነት ዋጋ ያጣ፥ መሪ የሆነውን ሰው ትዕዛዝ የሚቀበል ይጠፋል፥ እንኳን ግዳጅ ሊፈጽሙ የስልኩን ጥሪ እንኳን አያነሱለትም። አለ ሲባል እንደ ጠጉራም ውሻ አመራሩ ይከስማል። ይህ አካሄድ ለአማራ ትግል አይሆንም። የጋራ አመራርን መከተል ይበጃል።
በቅርብ ግዜ የሆነውን እናስታውስ እንጂ። ለምን ይመስላችኋል “ግንባር” ተብሎ ድንገት በጥቂት ሰዎች ከተፈጠረ በኋላ ፋሪዎቹ “እኛ ነን መሪዎቻችሁ ለኛ ከታዘዛችሁ ብር እንሰጣለን” ያሉት የት ደረሱ፤ ለትግሉ እንቅፋትና መከፋፈል፥ አንዱ ሌላውን እስከማፈንና መግደል ድረስ ያደረሰው ይህ ራስን የመⶄም አባዜ አይደለምንን? እባካችሁ ይህ መንገድ አይሰራም ብለን በሙሉ ልብ እንመንና የጋራ አመራር ላይ እናተኩር። ለእነዚያ ፋኖን በገንዘብ ለመግዛትና ከርቀት ለመቆጣጠር የሞከሩ ሰዎችን ፋኖን አልተረዱትም እና እሩጫቸውን ሲጨርሱ ደክመው ይቆማሉ ብለን እንደታዛቢ የውስጥ ምክር ብቻ ሰጥተን ሜዳ ላይ ወጥተን ሳንጯጯኽ ዝም አልን። ያልነውም አለቀረ በብርና በፕሮፓጋንዳ የሚገዛ ፋኖ ጥቂት ወይንም ሰነፍ መሪዎች ስለሆኑ በፍቅርና በዓለማ የሚመራው እጅግ ብዙ በመሆኑ ምክኒያት እንደተመኙት ጠቅላይ መሪና ንጉሥ ሆነው አማራን ተሳፍረው አራት ኪሎ ለመድረስ ብቸኛ ገስጋሽ አልሆኑም።
የአማራው ትግል መሪዎችና የትግሉ አወላለድ እንደ አክሊሉ ሀብተወልድ እንደነ ከተማ ይፍሩ፣ እንደ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ አርቆ የሚያስብ ሁሉን የሚሰማና የሚያሰባስብ እንደ ኮ/ል መንግስቱ ቆራጡ፣ እንደ አብይና መለስ ደግሞ በውሸትና በጥላቻ ተተብትቦ ራሱንም ሀገርንም ይዞ የሚወድቅ ሰው አይፈልግም። የተለየ ነው። ለህልውና የተነሳ ሕዝብ ነው። ይህን የህልውና ትግል ከግብ ማድረስና ዘለቄታዊነቱን ማረጋገጥ ከአሁኑ ሁለቱም የሚታሰብባቸው ግቦች በመሆናቸው የግለሰቦችን ራስ-ወዳድነትና ምኞት ለማባበልና ለመሸከም የሚሆን ትግል አይደለም። ብዙ የአመራ ልጆች አእምሮ በጋራ የሚመክርበት የጋራ አመራር ይሻል። የፈለገውን እያሠረ፥ እየገደለ፥ በሚዲያ ራሱን እየሸጠ፥ በገንዘብ ሰው እየገዛ የሚሄድ ከሆነ ትግሉ ለአማራ ህልውና የሚጠቅም አይሆንም። ወደ ባስ አዘቅት ይመራዋል።
የፋኖ ፈተና ድርብርብና ብዝኃነት ያለው ውጤት ማስመዝገብ የሚጠበቅበት የክንድ እና የአእምሮም ነው። አብይን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን እንድ መቶ ሀያ (120) ሚልዮን ህዝብንም አመኔታንና ነጻ አውጪዬ ነው ብሎ እንዲያስብ ማድረግ መቻል ነው። አማራ ሌሎችን ነጻ ላውጣ ብሎ ሳይሆን የራሱን ህልውና ማረጋገጥና ለዘለቄራዊነት ዋስትና ለመስጠት በልሂቃን አእምሮአቸው እየታጠበ፥ በሐሰት ትርክት በጥላቻ እየሰከረ፥ ከውጭ ተረልዕኮ እየተቀበለ የሚዘምትበት ማኅበረሰብና የጎረቤት አገር እንዳይኖር ማድረግን ይጨምራል። በዚህ ምክኒያት ሌላን ነጻ ላውጣ ብሎ ሳያቅድ የራሱን ህልውና ማስጠበቅ በራሱ የሌሎች ነጻነት ሆኖ መከሰቱ ይግድ ነው።
ማንም ስለኢትዮጵያና ስለለሌሎች ማኅበረሰብ ነጻነት ማሰብ “አዘናጊና አማራን ያስበላ ነው” ብሎ የሚያዘናጋ ቢኖር የኦነግን የሕወሃት ሤራ ሰለባ የሆነ ፕሮፓጋንዲሰት ነው። የአማራ ህልውና የታጠቁና የተደራጁ ጠላቶቹን በክንዱ ካሸነፈ በኋላ ለ50 ዓመታት በጥላቻ እንዲያዩት የተደረጉትን ወገኖቹን ከዚህ በሽታ መፈወስ ነው፥ ብሎም ዳግም አንዲህ አይነት ሁኔታ በኢትዮጵያ እንዳየከሠት መሥራት ነው። ይህ ረዥም ጉዞ ነው። በዚህ ጉዙ ገና ቃታ የሚስብ ተዋጊ መካከል እኔ ልንገሥ ብሎ የሚነሳ ሰው ቢኖር የሚከተሉት የሰብእናና የዓለማ ችገሮች ያለበት ሊሆን ይችላል፦
፩) የትግሉን ውስብስብነት ያልተረዳ እና ለውስብስቡ ጉዞ የሚያስፈልገውን የአመራር አይነት መረዳት ያልቻለ፥ ራሱን በማየውቅ መንገድ ላይ ብቁ መሪ ነኝ፥ ከእኔ የተሻለ ሰው የለም ብሎ የሚያስብ እጅግ ትዕቢተኛ ሰው ሊሆን ይችላል፤
፪) መምራት ብችልም ባልችልም ሰው እስከ ታዘዘልኝ ድረስ በሌሎቹ ችሎታ ሥር ተደብቄ ለሥልጣን እበቃለሁ፥ ሥልጣን ሊያስገኝ የሚችለውን ዝናና ቁሳዊ ጥቅም እሸምታለሁ የሚል ራስ ወዳድ፥ ለወንድሞች ሞት፥ ለሕዝቡ ትግል ዘለቄታዊ ውጤማነት የማይጨነቅ ፋኖ ውስጥ የሚገኝ ሌላው አብይ አህመድ ነው፤
፫) ከዚህ ትግል ውጭ ሌላ ሕይወት መኖር የማይታየው፥ ሌላ የሕይወት ትልም ያልበረውና ትግሉን እንደ እድል አድርጎ የሚወስድ እጅግ ሰነፍ ሰው ነው፤
፬) በትግሉ ሂደት ብዙ ወንድሞቹን አደጋ ላይ የታለ፥ ያስገደለ፥ ብር ሰብስቦ የበላ፥ ከመምራት ተወግዶ ተራ ከሆነ በወንጀል የሚየጠየቅ የሚመስለው ሰው ሊሆን ይችላል፥
፭) በሤራና ትግልን በማጨናገፍ፥ መከራን ለ50 ዓመታት በማዝለቅ የሚታወቁት የሕወሃትና የኦነግ/ኦሮሜማ/ብልጽግና ወይንም የምእራባውያን የስለላ ድርጀት ጋር እተነጋገረ ሥልጣን ያዝና እንረዳሃለን ብለው ከአማራ ሕዝብ የህልውና ትግልና ዘለቄታዊ ነጻነት በተቃራኒ የቆሞ ቅጥረኛ ነው።
ስለ ሕዝባችሁና ጓዶቻችሁ በፈቃዳች፥ በኅሊና ምሪትና በሰው ልጅ ፍቅር፥ ስለ ፍትሕና ስለ አውነት መከራ የምትቀቡሉ የፋኖ አኅት ወንድሞቻችን ሆይ፥ ፋኖ እስካሁን በሕዝብ አመኔታ አግኝቶ የዘለቅ አንድ በግል ምግባሩና ጠባዩ ሊወቀስ የሚችል መሪ ያልነበረው በመሆኑ ነው።
ረሃብና ጥም ቢጸናበትም ወደ መዝረፍና ወደ መስረቅ ያልወረድ እንደ ኦነግና ሌሎች ያልሠራውን የማያችድ የተባረኩ የአማራ ልጆች በብዛት ስላሉበት እና ጥቂት ጋጠወጦች ብዙዎች መልካሞች ስለተሸፈኑ ነው። መሪ ሲመጣ ያለፈ ታሪኩ፣ ድክመቱ፣ ህጸጹ፣ የመሪው ብስለትና ስህተት ሁሉ፥ ዳሕፀ ልሳን ሳይቀር ዩድርጅቱ ህጸጽ ሆኖ ይታያል። የመንግስት ህጸጽ የኢሰፓ ነው የሆነው፣ የመለስ ዜናዊ ጸረ ኢትዮጵያዊነት የኢህአዴግ ነው የሆነው። የአብይ ውሸት ጸረ አማራና ጸረ ኦርቶዶክስ ዕሳቤ የብልጽግና ፍልስፍና ነው የሆነው። የዚህ መድኀኒቱ የጋራ አመራርና ሲሆን ሰብሳቢውን በየ ስድሰት ወሩ አስቀድሞ በሚዘጋጅ የታወቀ መሥፈርት እየገመገሙ ማስቀጥላ መቀያየር መቻል ነው።
ለግዜው የሚያስፈልግ አመራር፦
ስለዚህ :- መሪ ሆኖ የሚመጣም የሱ ድክመትና ችግር የድርጅቱ ይሆናል የህዝብን ድጋፍ ያሳጣል። ስለዚህ ይሄንን እኔ መሪ ልሁን የሚለውን ይህንም ሩጫ ትታችሁ ምክርቤት አቋቁማችሁ የጋራ ኮሚቴ ፈጥራችሁ ተዘዋዋሪ የሆነ ሰብሳቢ ሰይሙ። ይህ አንደኛ የተለያዩ ሰዎችን ማሰባሰብ የሚችል ከታችም ከላይም ይወጣልና በሙከራው ግዜ በጎ የሰራ የንጹሀኑ ታማኝነት ያገኘ ካለ ለተወሰነ ግዜ ያውም ከስድስት ወር ባልበለጠ ግዜ እንዲያገለግል ከዛ እምነት ካገኘ ለሁለተኛ ግዜ ብቻ የሚመረት terms limitation ያለው ሰው ሊሆን ይችላል።
የኢትዮጵያ ፓለቲካ የሚፈርሰው መጀመሪያ እኔ ሊቀመንበር ልሁን እንሁን በሚል ፍጅት ነው። ትግሉ ሳያልቅ ቅንጅት እርስ በእርሱ ተናንቆ ፈረሰ።
ሀለተኛው ደግሞ ውረድ አልወርድም በሚል ሙግት ነው። አንድ ግዜ የተመረጠ ሰው እሺ ብሎ የወረደበት የፓለቲካ ስብስብ እስካሁን አልመጣም። ዋሽንግተን ላይ በነ ኮ/ል ጎሹና ኢህአፓው መርሻ ዬሴፍ የተመሰረተው ኢድኃቅ የተባለ ድርጅትን አስታውሱ። ከዛ ፓሪስ ላይ የተመሰረተው በዶክተር በየነ ጴጥሮስ የተመራው ስብስብ እነዚህ ድርጅቶች ሳይፈርሱ ሊቀመንበሩም ሳይወርድ ልክ እንደሌለ ይታሰብና ድርጅቱን ለሊቀንበሩ ትተው አዲስ ስብስብ ይፈጥራሉ።
ይህ ለሀምሳ ዓመት የቆየ ባህል ነው። አሁንም ፋኖ መሪ መረጠ ማለት ይህ መሪ ለዕድሜ ልክ መሪ ነኝ ብሎ ካሰበና ያወርዱኛል ያላቸውን ካጠቃ እንደ ተለመደው እሱንም ድርጅቱን ትተው የዛሬ ወር ሌላ ስም ያለው ስብስብ ይፈጥራሉ። አሁንም ምልክት በፋኖ መካከል አለ። ሸዋ፥ ጎንደር፥ ጎጃም አንድ አልሆኑም፥ አንድ ሆነው ሲገኙ አንዱን ራስ ወዳድ በብርና በፕሮፓጋንዳ ለይተው የሚጠቀሙ ይፈጠራሉ፥ አንዳንዶቹ ሌላውን ለመግደል እስከመሄድ ይሞክራሉ።
ስለዚህ ምክር የምትሰሙ ከሆነ መጀመሪያ አንድ ልጅ ሲወለድ ሁሉን ነገር በትንሹ ይዞ ነው። ትንሽ እጅግ ትንሽ እግር አይን ጄሮ ይዞ ነው። ልጁ ያለ ጆሮ ተወልዶ ቆይቶ ሲያድግ ያበቅል ይሆናል አይባልም። ድርጅትም ሲወለድ ዲሞክራሲያዊ አሰራር ማለትም አንድ መሪ ይመረጣል ይወርዳል፣ ሁሉም ሰው እኩል ዐሳብ አለው። መሪን መቃወም መብት እንጂ ጸረ ድርጅታዊነት አይደለም፣ ውሳኔ በክርክር ከተቻለ በአብላጫ ድምጽ ክፍል እንጂ ሊቀመንበር ያለው ሁሌም ትክክል ነው በሚል እሳቤ አይደለም። እንደ ፋኖ ያለው ንቅናቄ መመራት ያለበት አስድሞ በጽሑፍ የተዘጋጀ ፍኖተ ካርታ (የመሄጋ ጎዳና)፥ ጎዳናው ላይ የሚሄድበት አካሄድ (መርህ)፥ መርሁ የሚጠበቅበት አሠራርና መዋቅር፥ በዚህ ፍኖተ ካርታ ላይ መምራት የሚችሉ መሪዎች ሰብእና፥ የሞራል ልዕልና፥ እምነትና ታማኝነት፥ ጀግንነትና መስዋዕትነት የመሳሰሉ እሤቶችን በግልጽ ጽፎ ማስቀመጥና መከተል መቻል አለበት።
ነገር ቢበዛ ባአህያ አይሆንም ይላልና አባቶች። ሊቀመንበር መሆን የሚያጓጓው ሰው ካለ እንዳትመርጡት። ቦኋላ የሰቀሉትን ማውረድ የቻለ የኢትዮጵያ ስብስብ የለምና።
ሁለተኛ የኮሚኒስቶቹን የሊቀመንበርና የታዛዥ ዕሳቤን እርሱት። የአማራ ትግል የተቀደሰ ነውና በሰብእናቸው ቅዱሳን ለመሆን የሚመኙት ሊመሩት ይገባል። “እኔ” ማለት ለሃምሳ ዓመት ውርደት ቀለብ ያደረን ዕሳቤ ነው። ስለዚህ ሊቀመንበር አይኑራችሁ።
ይህ ምክርቤት ወይንም ማዕከላዊ የአመራር ቡድን መሆን ነው ያለበትን። ምክርቤት ውስጥ የሁሉም ድምጽ መሰማት አለበት። ይህ ከሆነ አንድ ሆኖ የተመሠረተው ፋኖነት ወርዶ የሸዋ፣ የጎንደር፣ ዩጎጃም፣ የወሎ አይባልም ነበር። ፋኖ አንድ ነበር፥ ራሳቸውን መሪ ነን ያሉ ሰዎች መፈጠራቸው ነው ወደ ክፍለ ሀገር ያወረደው። ከአዲስ አበባ ዝምተው፥ ከአውሮፓና አሜሪካ ተንቀሳቅሰው የተዋጉት ፋኖዎች በአዲስ አበባ ብቻ ተሰብስበው መቀመጥን የግድ የሚያደርግ አካሄድ ነው የተፈጠረው። ከወሎም፣ ከጎንደርን፣ ከሸዋም፣ ከሸዋም ከመጡ የፋኖ አባሎች ግብር ተቀላቅለው የነሩትን ባዕድና ባይተዋር የሚያደርግ “የእኔ ልንገሥ” እንቅፋት ነው። ራስ-ነገሥ መሪዎች ሲመጡ ነው ክፍለ ሀገር የተፈጠረው። ስለዚህ ከራሳችን ዝና በላይ ካሰብን ውጤት እናመጣለን ለራሳችን ዝና ካሰብን ግን መንገድ ላይ እንቀራለን።
ፋኖ ሀሳቡ ሲጠነጠን የተወሰኑ ሰዎች ገዳም ገብተው ነበር። ከሱባኤ ቦሏላ ሲወጡ አንድ የበቁ አባት አገኟቸውና “ልጆች ስለ ኢትዮጵያና ስለ ሰው ልጅብ መብትና እኩልነት፥ ስለ እውነት፥ ስለ እግዚአብሔር ስም ክብር ብላችሁ ከሰራችሁ ይሳካላችሀል፣ በኢትዮጵያ እና በእግዚአብሔር ስም ለራሳችሁ ጥቅም ካሰባችሁ ግን አይሳካላችሁም” አሉ።
በእውነት በእሽቅድምድም፣ እራስን አንቱ ለማለት ሩጫ ውስጥ ገብተን እራሳችንን ከኢትዮጵያና ከእግዚአብሔር ካስቀደምን አይሳካልንም። ከድል በኋላ አገር ተረጋግቶ፥ ፍትሕ ሰፍኖ፥ አገርና ሕዝብ መተማመን ላይ ደርሶ፥ ትውልድ ከስሑት ርእዮትና ሐሰተኛ ትርክት መርዝ ተገላግሎ ሰላማዊ ፖለቲካ ሲጀመር በታወቀ የአገር ሕገ ምንግሥትና የሕዝብ ራዕያና ፍላጎት አንጻር “እኔን ምረጡኝና የፈለጋችሁ ቦታ አደርሳችኋለሁ” ብሎ መወዳደር ይቻላል። አሁን ግን መንገዱ የተለየና የብዙ ሰው አእምሮና የጋራ ውሳኔ የሚፈልግ አሳታፊ፥ በፍቅርና በመተማመን የሚመራ፥ ማንን ነፍሱን ለመስጠት ከቤቱ የወጣ ፋኖ ቅር የማይሰኝበትና “የተከድቻለሁ ወይንም የጥቂት መጠቀሚያ ሆኛለው” የማይልበት አመራር ይፈልጋል።
እግዚአብሔር በኢትዮጵያ ላይ ሙገሳውን (Credit) እንዲወስድ የፈቀደለት ሰው የለም። ሁሌም እኛ ባላሰብነው ባላቀድነው መንገድ ነው ያለውን የሚያፈርሰው። እስቲ እንያቸው፥ ኢህአዴግ ታግለን አሸነፍን ብሎ ሙገሳውን (Credit) መውሰድ የሚችለው? ደርግ የወደቀው በክህደቱ፥ በደም አፍሳሽነቱ እና የኢትዮጵያን ሰው ከአብዮቱ በታች ነው ብሎ እግዚአብሔርን ንቆ ሰብእናን ስላዋረደ አይደለም? ወያኔ የወደቀው በቄሮና በአማራ ወጣት ጩኸት ብቻ ነው? አይደለም ጥቂታ ሳሉ ብዙኃኑን ለ30 ዓመት እያባሉና መሳያቸውን ፈጥረው እግዚአብሔርን እጅግ ስለበደሉት ነው። የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ ያለው መዝሙረኛው ዳዊት በኢትዮጵያ ላይ ነው ሠራው። የአድዋ ድል የሞሶሎኒን ሥርዓት እዚህ ሲመጣ እዛው አውሮፓ ላይ አፈረሰው። ማን ሮምን ማፍረስ የሚችል ሀይል ነበረው። የሁለተኛው አለም ጦርነት በተነሳ በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ሮም ፈረሰ። የኢትዮጵያ ጦር ነው ሄዶ ያፈረሰው። አይደለም፥ የኢትዮጵያ አምላክ ነው።የሱማሌ ጦርነትን ደግፈው የተነሱት የግብጹ ስልዳትን ማን ጥይት በደርግ የተተኮሰ ነበር? ከተተ፣ የኢራኑ ሽህን ማን ገለበጠው? ማን ሶቭየት ዩኒየንን ያዘጋጀውን የሱማሌ ጦር ትቶ ታንኩን ወደ ሱማሌ እንዲያዞር ያደረገው። እነ ሀምሳ አለቃ ለገሰና እነ ሻለቃ መንግስቱ፣ ማን ለመቶ ዓመት የቤት ስራ ሰጥተናቸዋል ያሉትን ሻቢያና ወያኔ አስተናነቀ፣ ማንስ ኢህአዴግን አፈረሰ? አሁንስ ሱዳንን አተራመሰ?
እግዚአብሔርን የማያውቅ ወይንም ራሱን ብልጥና ብልህ አስመስሎ ሥራውን የሚዘነጋ፥ ታሪክ ሠሪነቱን የሚያቃልል “ምረጡኝ፥ እሻላለሁ፥ ድል አመጣለሁ–ወዘተ” እያለ ፈጣሪን ያሳዝናል፥ ትግሉእነ የሰው ብቻ ያደርገዋል። የዚህ አይነት ሰው ጉጉ ለሥልጣን ይሆናል። በዚህ ሀገር ላይ ከእግዚአብሔር በቀር የምንመካበት መሪ አይኖርም። ስለዚህ በፈቃዱ መጠቀሚያ ቢያደርገን እንኳን ብለን፥ ጓዶቻችን የግድ ሱሉን መሆን አለብን። በኛ ብልጠት፣ በኛ ብር፣ በኛ ተንኮል፣ በኛ ቲፎዞ ብዛት ታሪክ ሰሪ አንሆንም።
አደራ ለፋኖዎች፦ የተቀደሰውን በሥልጣን ሽሚያ አታርክሱት
ወድም እኅቶቻችን ከዚህ የአመራን የተቀደሰ ትግል ከሚያረክስ ጠባይ ውጡ። ማኒፌስቶ ጽፈው፥ ከባዕዳን ጋር ሤራ ሸርበው፥ የተንኮል ትግልን ከፍልሥጤም፥ ከኮሚኒሰት ቻይና፥ ከሙንሼቪክና ቮልሼቪክ፥ በዓለም ላይ የሚታወቁ ተንኮሎችን ሁሉ አጥንተው አማራ የተባለ ክፍለ-ሕዝብ፥ ኢትዮጵያ የተባለች ታሪካዊት አገርንና ኦርቶዶክሳዊት ክርስትናን፥ ነባር ባህሎችንና እምነቶችን ዒላማ አድርገው ወደ ትግል የገቡት ሻዕብያን፥ ሕወሃትንና ኦነግን አትምሰሉ። ከእነርሱ ምንም ትምህርት እትቅሰሙ! እናንተ የጀመራችሁት ትግል የእግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር የፈጠረውን ሕዝብን፥ እምነቶቻቸውን፥ ታሪካቸውንና ርስታቸውን ለመከላከል የተላካችሁ እንጂ ሤረኞች አይደላችሁም።
አንድ አሜሪካዊ “እግዚአብሔር ፈገግ ማለት ሲያምረው የሰውን የነገ እቅድ ያዳምጣል” ብሏል። ነገ እንዲህ አደርጋለሁ፣ የዛሬ ዓመት እንዲህ እሆናለሁ ሲል ነገ ፈጣሪ ያስቀመጠለትን አላወቀም ብሎ ፈገግ ይላል ለማለት ነው።
በወንጌልም እንዲህ የሚል ይገኛል “ምሳሌም ነገራቸው እንዲህ ሲል፦ አንድ ባለ ጠጋ ሰው እርሻ እጅግ ፍሬያም ሆነችለት። እርሱም፦ ፍሬዬን የማከማችበት ስፍራ አጥቻለሁና ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ አሰበ። እንዲህ አደርጋለሁ፤ ጐተራዬን አፍርሼ ሌላ የሚበልጥ እሠራለሁ፥ በዚያም ፍሬዬንና በረከቴን ሁሉ አከማቻለሁ፤ ነፍሴንም፦ አንቺ ነፍሴ፥ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፥ ብዪ፥ ጠጪ፥ ደስ ይበልሽ እላታለሁ አለ። እግዚአብሔር ግን፦ አንተ ሰነፍ፥ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል፤ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል? አለው። ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው። “ (ሉቃ 12-16-21 )
ስለዚህ፣
፩ኛ ምክር ቤት ምረጡ፦
፪ኛ ፋኖ አንድ ሆኖ ነው የተወለደው ይህንን የክፍለ ሀገር ክፍፍልን የፈጠርነው እኛ መሪዎቹ ነን ብላችሁ አስቡ፣
፫ኛ፣ አንድ መሪ እንዳትመርጡ።
ፋኖ በማኦ፣ በስታሊን፣ በመለስ፣ በመንግስት አምሳል የሚወለድ መሪ አያስፈልገውም። ስለዚህ የጋራ አመራርና ተዘዋዋሪ ሰብሳቢ ፍጠሩ።
፬ኛ፣ የአዲስ አበባ፣ የባሌ የወለጋ የብዙ ክፍለሀገራት ፋኖ እየተፈጠረ ስለሆነ ምክር ቤት ከሆነ በሩ ክፍት ይሆናል የነሱን ትግልና ድምጽ ይጨመራል።
፭ኛ መሪ ማውረድ ድርጅት ያፈርሳልና የተመረጡ ሰዎች የስራ ግዚያቸው ከ6 ወር መብለጥ የለበትም። መሪ ለእድሜ ልክ በፋኖ ውስጥ አይሰራም።
እግዚአብሔር ከናንተ ጋር ይሁን። እግዚአብሔር እና ኢትዮጵያን አስቀድሙ። በእውነተኛው መንገድ ካልሄዳችሁ አይሳካልችሁም። ቢሳካ ስንኳ ሌላ ዙር የሕዝብ መከራ ታመጣላችሁ።
ትዝብትና ምክር ቁጥር ፪ ከትንተና ጋር በሳምንት ይደርሳችኋል።
ፈጣሪ ያቆየን