በህግ አምላክ! ክርስትናና እስልምና ምን ጠቀመን?

ያሬድ ኃይለመስቀል.

Yaredhm.yhm@gmail.com

የኢትዮጵያ ታሪክ ከክርስትና; ከእስልም እና ይሁዳዊነት (Judaism) እምነትቶች ውጪ ማሰብ አይቻልም? ማሰብ ይቻላል የሚል ካለ ቢያስተምሩን በጎ ነው።

የኢትዮጵያ እምነቶች ጥቅማቸው በጣም ብዙ ነው፤ አንድ መጽሀፍም አይበቃውም፤ ለቅምሻ ያህል የኢትዮጵያ እምነቶች ለነጻነት፤ ለፍትህ፤ ለትምህርት፤ ለብልጽግና፤ ለስነ ህንጻ፤ ለህክምና፤ ለሰላም፤ ለታሪክ፤ ለስነ ጥበብ፤ ስነ እጽዋት፤ ስነ ፍጥረት፤ ስነ ከዋክብት፤ ስነ ቀመር፤ ስነ ፍልስፍና፤ ስነ ምግባር ያበረከቱትን በአጭር በአጭር እንይ።

መጽሀፍ ለሚያነብቡ ስዎች መቼም ሀገርን ከተቋም ውጪ ማሰብ እንደ ትልቅ ደፋርነት እንጂ እንደ እውቀት አያዮትም። የኢትዮጵያ እምነቶች ቤተ እምነት ብቻ ሳይሆኑ ተቋማትም ነበሩ።

1. ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለሺ አመታት ብትኖርም እስከ መስከረም 14 1900 ድረስ የመከላከያ ሚኒስቴር አልነበራትም ግን ለሺ አመታት እራሷን ተከላክላ ቆይታለች። ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ የመጀመሪያው የጦር ሚኒስቴር ነበሩ።

2. እስከ 1930ዎቹ ድረስ ኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስቴር አልነበራትም ይሁንና ትምህርት ለሺ አመታት ነበራት። ማን አስተማረ?

3. ኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴር እስከ 1930ዎቹ አልነበራትም ይሁንና እንደ “የህዳር ወረርሽን” (Spanish flue) ያለውን ተከላክላለች። ማን ተከላከለ?

4. መዘጋጃ ቤት እስከ ቅርብ ግዜ አልነበራትም ይሁንና ሰው ይወለዳል፤ ያድጋል፤ ሰው ሲሞት በስርአት ይቀበራል። ማን ይቀብራል?

5. መአከላዊ ፍርድ ቤት እስከ 1950ዎቹ አልነበራትም ይሁንና ወንጀለኛ የሚተዳደር ሀገር አልነበረችም። ማን ነበር ፍርድ የሚሰጠው?

6. የአራዳ ፓሊስ በአጼ ሚኒሊክ ቢቋቋምም መሀበረሰቡ ለሺ ዘመን “ፍትህና ወንጀል፤ ትክክልና ስህተት፡ መጥፎና ጥሩን” የሚመዝንበትና የሚፈርድበት የሀይማኖት ህግጋት ነበሩት።

7. ኢትዮጵያ ቤተ መዘክር እና  መዝገብ ቤት  በአጼ ኃይለስላሴ ግዜ ነው ተመሰረተ ይሁንና መዛግብቶች ለሺ አመታት ጠብቀው ያቆዮ ተቋማት ነበሯት።  ማን ጠበቀ?

እነዚህ ሁሉ ተግባራትን የሚያከናውኑት ተቋማት እነማን ነበሩ። ቤተ እምነቶች አልነበሩም። በተለይ የኦርቶዶክስ ሁለቱ የተወቀሱት ቤተ ክርስቲያንና የእስልምና እምነቶች አይደሉም ይሄንን ተሸክመው የኖሩት። ወደ ዝርዝሩ እንግባ።

1ኛ ነጻነት

ለምሳሌ Why Nations Fail በሚለው የ Daron Acemoglu and James A. Robinson መጽሀፍ ገለጥ ብናደርግ “ተቋም” ለአንድ ሀገር በነጻነት ለመኖር ብቸኛ መመዘኛ አድርገው ጽፈዋል። ለምሳሌ እነዚህ ጸሀፊዎች ኢትዮጵያንና ሱማልያን ያነጻጽሩና  በሱማልያ ውስጥ ተቋማት ተገንብተው ስላልነበረ አስተባብሮ ቅኝ ገዢዎችን መከላከል የሚችል ተቋም አልተፈጠረም ነበር ይላሉ። “The absence of cohesive and inclusive institutions made it easier for these colonial powers to exert their influence and impose their rule”። ይህ እንግዲህ በመላው አፍሪካ ታይቷል። ተቋም ያላቸው እንደ ዙሉ ንጉስ ያሉ ቢያንስ ቢያንስ ተዋግተው ተሸንፈው ነው የተገዙት። ብዙዎቹ ግን ምንም ሀይማኖታዊም ሆነ አለማዊ ተቋማት በግዜው ስላልነበራቸው አስተባብሮ ነጻነታቸውን ማስጠበቅ አልቻሉም።

በኔ እይታ ኢትዮጵያ አምስት ተቋማት ነበሩዋት። አንደኛ ንጉስ፤ ሁለተኛ የክርስትና ቤተእምነት፤ ሶስተኛ የእስልምና ቤተእምነት፤ አራተኛ የይሁዳዊነት ቤተእምነት፤ አምስተኛ ገበያ ናቸው። 

እነዚህ አምስት ተቋማት ናቸውን የኢትዮጵያን ነጻነት ያስጠበቁት። እነዚህ ተቋማት ባይኖሩ ህዝቡ ሀገሩ እንደተወረረ እንኳን የሚሰማበት እድል አልነበረውም። መረብ ምላሽ ላይ ጠላት ሲያርፍ ኢሊባቡር ባሌ ኦጋዴን የሚሰማው በቴሌቭዥን ወይንም በቲዊተር አይደለም።   ከዋናው ፓትሪያርክ እስከ አጥቢያ ድረስ ሰንሰለት ያለው እዝ ያለው ተቋም ነበር። በእስልምናም ከዋናው ኢማም እስከ አንድ አጥቢያ ትምህርት ቤት ድረስ የተሳሰረ ተቋም ነበር።  ንጉሶቹና ተጓዥ ንጉስ ስለነበሩ ቋሚ ቤተመንግስትም፤ ሞባዬል ስልክም የፓስታ ሳጥን ቁጥርም አልነበራቸውም።  ንጉስ ኖረም አልኖረም መስጊስና ቤተ ክርስቲያን ሁሉም ቦታ አለ። ለጅ ሲወለድ ክርስቲያኑ ያጠምቃል፤ እስላሙ መርቆ ቆጥሮ ልጁን ይንከባከባል፣ ፊደል ስላለው ያስተምራል፤  ሲሞት ደግሞ ቆጥሮ ለይቶ ይቀብራል እንጂ ለጂብ አይተወውም። ሀገር ሲወረር ጠላት ሲመጣ በቲዊተር ወይንም በቴሌቭዥን አልነበረም መለክት የሚነገረው። ነጋሪት ተጎስሞ ተዘጋጅ ታጠቅ ዝመት የሚባለው በቤተ እምነቶች ከዛም በገበያ ነበር።  በነጻነት መኖርን ጥቅሙ ካልገባን በስተቀር ታድያ የኢትዮጵያ ክርስትናና እስልምና ለኢትዮጵያ ምን አበረከቱ ብሎ ማቃለል  በዘንድሮ ወጣቶች እባባል “አረ ሼም ነው” ያስብላል። ለሺ አመታት የብልጽና ወይ የኢህአዴግ መዋቅርና ካድሬ ይሆን ተቋም ሆኖ ሀገር ያስጠበቀው?

2ኛ የትምህርት ሚኒስቴር

ሰው መቼም ጤነኛ አይምሮ ያለው ትምህርት ቤት መሰልጠን አይደለም ብሎ የሚያስብ ያለ አይመስለኝም።

ኢትዮጵያ እስከ 1940ዎቹ ድረስ የትምህርት ሚኒስቴር አልነበራትም ግን ትምህርት ቤቶች ነበሩዋት፣ ብልጽግና ቀረጥ ሰብስቦ ትምህርት ቤት ከፍቶ አይደለም ትምህርት ያስጀመረው።

ኢትዮጵያ እንደውም በአለም ላይ ትልቁ የጽሁፍ ክምችት ያላት ሀገር ናት። በወሎ፤ በጎንደር እና በሀረር ያለውን የእስልምና መጽሐፍት ሳይቆጠሩ በኦርቶዶክስ ቤተ እምነትዎች ውስጥ ብቻ ከ300 ሺ በላይ በብራና የተጻፏ መጽሀፍት አሏት። እኔ አይደለሁም ይሄንን የምለው፤ ጥናት ያሳተሙት ፕሮፌሰት ሪቻርድ ፓንክረስት ናቸው። ሶስት መቶ ሺ ምናላት የሚሉ የብልጽግና ካድሬ ካለ በንጽጽር እንየው።  ፕሮፌሰር ሪቻርድ ይህ 300ሺ ከኢሮፕያውያን ጋር ሲወዳደረው ኢሮፓውያን የዚህን 10 በመቶ ማለትም 30ሺ አልጻፏም ይላሉ። 

እነዚህ የብራና ጽሁፎች የጽሎት ብቻ አይደሉም። የሀይማኖት  (Theology) ፤ የታሪክ (History)፤ ገድል (Biography (እስቲ አስቡት የ12 ደቀ መዝሙሮች ከውልደት እስከ ሞት ተርጉሞ ጠርዞ ያስቀመጠ ሀገር አለ?); ስነ እጽዋት (Botany)፡ ስነ ከዋክብት (Astronomy): ስነ ህክምና (medicine)፡ ስነ ቀመር (Binary mathematics): ፍልስፍና (philosophy)፡ ስዕል (Painting)፤ እደ ጥበብ (Arts and Crafts): ቀለምና ማዘጋጀት (Chemistry): ሙዚቃ (Music)፡ መድሀኒት መቀመም (pharmacology)  ውዝዋዜ (choreography)፡ ስነጽሁድ (Literature): ኮኮብ ቆጠራ (numerology)፡ አርምሞ (meditation);  ቋንቋ (ግዕዝ አረብኛ፤ ግሪክ፤ ላቲን) (Languge)፤ ትርጉም (transilation)  ወዘተ። 

እነዚህ እውቀቶች ትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን ልዮ መሰልጠኛዎች ነበሯቸው (Sub specialization)።  ዜማ የሚማርና ትርጉም የሚማር በአንድ ትምህርት ቤት አይደለም። በዘመኑ የታወቁ እንደ አሁኑ ፕሮፌሰቶች በአንድ ነገር ላይ ጥልቅ እውቀት ያላቸው ሰዎች ያሉበት (Specialization) ትምህርት ቤቶች ነበሩ።  በዛ ዘመን እንደ አሁኑ በ C ወይንም በ 50%  ማለፍ የለም። አንድ ልጅ ሀሁን ሙሉ በሙሉ ሳያውቅ ግማሹን አውቋል ተብሎ አቡጊዳ አይሰጠውም።  እንግዲስ እንዲህ ጽድት ያለ የትምህርት ስርአት የነበረው ሀገር በትምህርት ሚኒስቴር ወይስ በነጻ የሚያስተምሩ ቤተ እምነቶች። ይህ እውቀት በነጻ በእስልምና እና በክርስትና ቤተ እምነቶች አይደለም። ታድያ በምን መመዘኛ ነው ይሄንን የዕውቀት ማመንጫ የነበሩ ተቋማት በምን ብቃት ነው ለማቃለል የምንሞክረው። አረ በህግ አምላክ?

እነዚህ የዚህ እውቀት ባለቤቶችስ በአለም ላይ ተፎካካሪ እንደነበሩ እስቲ ሁለት ሰዎችን እንይ።  አንደኛው አባ ተስፋጽዮን ይባላሉ። ሁለተኛው ዲያቆን ሚካኤል ይባላል። አባ ተስፋጽዮን ደብረ ሊባኖስ በግራኝ መሀመድ ሲፈርስ ተሰደው ወደ ሮም የሄዱ ምሁር ናቸው።  እኛ እምነት ምን ሰራልን ስንል የካንብሪጅ (Cambridge) ዮኒቨርስቲ ደግሞ የኢትዮጵያ መንኩሴና ዲያቆን እንዴት በኢሮፕ እምነት ላይ ተጽዕኖ እንዳሳረፏ መጽሀፍ ጽፈው ኣንድ ወር ቦሀላ ገበያ ላይ ይውላል። የመጽሀፏ አጭር መግለጫ በእንግሊዘኛ እንዲህ ይላል።

This Element examines the life and legacy of the sixteenth century Ethiopian intellectual Täsfa Ṣeyon. It reconstructs his formative years in the the Horn of Africa and his diasporic life in the Holy Land and Italian peninsula, where he emerged as a prominent intermediary figure at Santo Stefano degli Abissini, an Ethiopian monastery within the Vatican. He became a librarian, copyist, teacher, translator, author, and community leader, as well as a prominent advisor to European humanist scholars and Tridentine Church authorities concerned with the emerging field of philologia sacra as it pertained to Ethiopian Orthodox (täwahedo) Christianity. We reconstruct his wide-ranging contacts with the Roman Curia and emerging orientalist academy, and then scrutinize his editio princeps of the Ge’ez Gospels. A final section traces his modern influence, erasure, and rediscovery by later generations of Western orientalists, Ethiopian writers, and Catholic thinkers.

አንድ ከደብረሊባኖስ ወደ እስራኤል ከዛ ወደ ቫቲካን የሄዱት አባ ተስፋጽዮን የፈርንጅ ትምህርት ሳይማሩ የኢሮፕ Humanist Scholar መስራች እንደሆኑና እንዴት ኢሮፕን እንደቀየሩ ይናገራል። መጽሀፏ በDec 12, 2024 ስለሚወጣ ግዙት።

https://www.cambridge.org/core/elements/abs/many-lives-of-tasfa-soeyon/E18E06F8FB5C91EDEF4286FBD448F1D8

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት በካቶሊክ እምነት ላይ ያሳረፈችውን ተጸኖና እንዲሁም በማርቲን ሉተር ተሀድሶ ንቅናቄ ላይ ተጸኖ እንደነበራት Ian Campbell, Holy War: The Untold Story of Catholic Italy’s Crusade Against the Ethiopian OrthoDdox Church ብሎ ባሳተመው መጽሀፍ ውስጥ አባ ተስፋጽዮን በካቶሊክ እምነት ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንዳሳደሩና የካቶሊክም እምነት ከኢትዮጵያ 81 መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን 73ቱን እንዲቀበል እንደረጉ ያመላክታል። ይህም በThe Council of Trent in 1546 በሚባለው ላይ 73 መጽሐፍት ተቀባይነት እንዳገኝ ተገልጻል። 

የማርቲል ሉተርን 1517 ተቃውሞ ተከትሎ አባ ተስፋጽዮን ለካቶሊክ ቤተክርስቲያን ዋነኛ መከላከያ መሳርያ ሆነው ነበር ብሎ  ኢአን ካምፔል ጽፏል (“he saw Ethiopianist scholarship as a useful intellectual weapon in the unfolding politico-relgious showdown with the Protestants) ።  ይህ የካቶሊክና የኦርቶዶክስ መቀራረብ ወዲያው ፓርቹጋሎቹ መጥተው ንጉሱን ወደ ካቶሊክ ስለቀየሩት ልዮነቱ በጦርነት ሻከረ እንጂ በዛው ቢቀጥል ኖሮ ምናልባትም ካቶሊክ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ላይ ከሚኖረው ተጽዕኖ በላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት በካቶሊክ እምነት ላይ ከፍ ያለ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችል ነበር። (ይህ Ian Campbell መጽሀፍ Hilton Hotel አለ ገዝታችሁ አንብቡት በጣም የማናውቃቸው ታሪኮች አሉት)። 

በሌላ በኩል ደግሞ ማርቲል ሉተት ኢትዮጵያዊውን ዲያቆን ሚካኤል የሚባልን በ1534 በዊተንበርግ ጀርመን ተነጋግረው ማርቲን ሉተር የሱ ተቃውሞ በመጀመሪያይቱ የክርስቲያን ቤተ እምነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ላይ አስተምህሮ የታገዘና ያደረገውም ትክክል እንደሆነ ጽፏል። 

Martin Luther’s Fascination with Ethiopian Christianity፡ https://www.christiancentury.org/blog-post/guest-post/martin-luthers-fascination-ethiopian-christianity

ከዲያቆን ሚካኤል ጋር ከተገናኘ ቦሀላ ማርቲን ሉተር ይሄንን ጽፋል “Ethiopian Christians practiced elements of the faith absent in Roman Catholicism, elements Protestants would later adopt: both bread and wine at Communion, vernacular Scriptures and married clergy. Absent from Ethiopian Christianity were practices Protestants would dismiss: the primacy of the Roman pope, indulgences, purgatory, and marriage as a sacrament. Luther’s theological fascination with the Ethiopian Church was illuminated in 1534 in his face-to-face dialogue with an Ethiopian cleric, Michael the Deacon, in which Luther tested out his theological portrait of the Ethiopian Church.

Recalling the dialogue with Michael the Deacon, Luther later stated: “We have also learned from him, that the rite which we observe in the use of administration of the Lord’s Supper and the Mass, agrees with the Eastern Church. … For this reason we ask that good people would demonstrate Christian love also to this (Ethiopian) visitor.”

እንግዲህ እነዚህ ሁለት ሰዎች እንደ አጋጣሚ ከሀገራቸው ወጥተው ሀሳባቸውን በመግለጻቸው ፈረንጆቹ ከአምስት መቶ አመት ቦሀላ እየቆፈሩ እያወጡ እንዴት በኢሮፕ ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደሩ መጽሀፍ እየጻፏ ነው።  እና ሀገር ደግሞ ክርስትናና እስልምና ምን ጠቀሙን የሚሉ ድፍረቶች ተነስተዋል።

የአፍሪካ ህዝብ በ1800 ዓመተ ምህረት 85 ሚሊዮን ይገመት ነበር። ከዛ ውስጥ 12 ሚሊዮኑ ታፍኖ ተወስዶ በአሜሪካ ባርያ ተደርጓል።  እኛ ለምን እንደ ምዕራብ አፍሪካው በቀላሉ አልተጫንም ካልን ተቋማት ነበሩን። አስባስበው የሚያዋጉን።  እነሱም ዋነኞቹ ቤተ እምነቶች ነበሩ።

በክፍል ሁለት የኢትዮጵያ እምነቶች እንዴት የፍትህ፤ የጤና፤ የመሀበራዊ ጉዳይ እና የበርካታ ሚኒስቴሮች ተቋማት ሆነው እንደሰሩ ያሳያል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *