ያሬድ ኃይለመስቀል
የእልፍኝ “ምሁራን”
ሲሳይ አጌና ከዶ/ር ብርሀኑ ነጋ ጋር ያደረገውን ቃለ መጠይቅ አዳመጥኩ። የዶክተር ብርሀኑን ቃለ መጠይቆች ሳዳምጥ በፍቅር እስከ መቃብር ውስጥ ያሉትን የቄስ ሞገሴን ገጸ ባህርይ ያስታውሰኛል። ለነገሩ ይሄንን ሀሳብ ጭንቅላቴ ውስጥ የከተተው አንድ ወጣት ነው። ይህ ወጣት አባቱ እዚህ እንግሊዝ ሀገር ይዞት ሲመጣ ትንሽ ልጅ ነበር። ይሁንና ቤተሰቦቹ በሀገር ጉዳይ ላይ ጽኑ ተሳታፊ ስለነበሩ ጥሩ አንባቢና አስተዋይም ሆንዋል። አንዴ ዶ/ር ብርሀኑን ቄስ ሞገሴ ብሎ ሲጠራው ሰማሁና ማናቸው ቄስ ሞገሴ አልኩት?
ቄስ ሞገሴማ የፊታውራሪ መሸሻ ነፍስ አባት ናቸው አለኝ። የነፍ አባት ስራ ተቆጪ፣ መካሪ እና አስተማሪ ነው። ቄስ ሞገሴ የነፍስ አባት ይሁኑ እንጂ ፊታውራሪን መሸሻን ከማረም፣ ከመገሰጽና ከማስተካከል ይልቅ ፊታውራሪን የሚያስደስታቸውን ነገር ብቻ እየፈለጉ የሚያሽቃብጡ ናቸው አለኝ።
ከፍቅር እስከ መቃብር ውስጥ ጉዱ ካሳን፡ ፊታውራሪ መሸሻን፡ በዛብህ እና ሰብለ ትዝ የሚሉኝ። ቄስ ሞገሴን ትዝ ስላላሉኝ እሳቸውን ፍለጋ የወጋየሁ ንጋቱን ትረካ አዳመጥኩት። ቄስ ሞገሴ ደራሲው አዲስ አለማየሁ የምሁራንን አድርባይነት ለመግለጽ የፈጠሩዋቸው ትልቅ ገጸ ባህሪይ ሆነው አገኘሁዋቸው። የኛ ሀገር ሳንቾ ፓንዛ ናቸው። ጉዱ ካሳ ‘….አባ ሞገሴ እንደምታውቋቸው የራሳቸው ሀሳብ የሌላቸው፤ የሰውን ሀሳብ ብቻ ካይኑና ከግንባሩ አይተው ለመተርጎም ችሎታ ያላቸው። ሆዳቸውን የሞላ በፈለገው መንገድ የሚመራቸው፣ተግባራቸውን ለሆዳቸውን የሸጡ የለወጡ ናቸው። ያስቅባቸዋል።
ለምሳሌ ፊታውራሪ በዛብህን አስጠርተው የሰብለ ወንጌል ትምህርቷ እንዴት ነው ብለው ሲጠይቁት፣ በዛብህ ሰብለን “እሳቸው” ማለት ሲገባው “እሷ” በማለቱ ፊታውራሪ ቱግ ብለው “በል… ጠጣና ውጣ!” ብለው አቋረጡት።
በዛብህ የተባረረው ለአንድ ቀን ይሁን እስከመጨረሻው ስላልገባው በማግስቱ ወደ ፊታውራሪ ቤት አልሄደም። ፊታውራሪም ነገሩ ስለከነከናቸው “ይህ የገበሬ ልጅ፣ ልጃችንን አስተምርልን ብለን ብናከብረው ተናገርከኝ ብሎ አኩርፎ መቅረቱ ነው ሲሉ”። አባ ሞገሴ ቀለብ አድርገው “ወዲያውስ ጌታ ሲቆጣ ደስ ያሰኛል እንጂ ያስቀይማል፣ ጌታ ባለሟሉን ነው መቼም የሚቆጣው…” አሉ ቄስ ሞገሴ።
በሌላ ቀን ደግሞ ባላገሮች ሰብላችንን በረዶ ስለመታው ተቸገርን፣ የደንቡን እንጂ ተጨማሪ የእጅ መንሻ፤ የዐመት በዓል ፍሪዳ ማቅረብ አንችልም እና ይማሩን ብለው ሽማግሌ ይልካሉ። ፊታውራሪ ቱግ ዘምቼ ጎልቴን አስከብራለሁ ይላሉ። ፊታውራሪ ድሮ ጀግና ይሁኑ እንጂ አሁን የ70 ዓመት ሽማግሌ ናቸው። ተቆጥተው ዘምቼ፣ ቀጥቼ፣ ዘርፌ እመጣለሁ ብለው ሲቁነጠነጡ ባለሟሎቻቸው እነ ቀኛዝማች አካሉ፣ እነ አዛዥ ደስታ፤ እነ ብላታ፣ እነ ባላንባራስ ምትኩ ፊታውራሪ ገበሬ አንዳይገላቸው ሀሳባቸውን ለማስቀየር ሲያባበሏቸው ቄስ ሞገሴ እንደተለመደው የፊታውራሪን ፊት አይተው ጥልቅ ይሉና።
“ቀድሞ ጌቶች ባላገርንና ወይፈንን አነጻጽረው የሰጡት ጥሩ ምሳሌ የማይገኝ ትክክለኛ ምሳሌ ነው፣ ወይፈን ዛርላ እንጫንብህ ሲሉት እንቢ በማለቱ የተለቀቀ እንደሆነ ሁለተኛ አንገቱን አያስነካም። አሁንም እነዚህ ባላገሮች እንዲህ ያለ የድፍረት ንግግር ተናግረው የተለመደ እዳቸውን አንከፍልም በማለታቸው የተለቀቁ እንደሆነ ሁለተኛ ግብር ክፈሉ ብሎ ደጃቸው የሚሄድ የለም አሉ ቄስ ሞገዜ የፊታውራሪ አይን እየተመለከቱ”
ጉዱ ካሳ በቄስ ሞገሴ ተናዶ በመሀከል ገብቶ ‘….አባ ሞገሴ እንደምታውቃቸው የራሳቸው ሀሳብ የሌላቸው፤ የሰውን ሀሳብ ብቻ ካይኑና ከግንባሩ አይተው ለመተርጎም ችሎታ ያላቸው። ሆዳቸውን የሞላ በፈለገው መንገድ የሚመራቸው፣ተግባራቸውን ለሆዳቸውን የሸጡ ተለወጡ ናቸው። እሀሀሀ!!!! ። ታድያ ጳጳስ የሆነ ሰው የኚህን ስልጣን ገፎ ዛሬ እርሶ (ቀኛዝማች) እንደሞከሩት በቅን መንገድ ለሚመራ ሞግዚትና መስጠትና እሳቸውን የእልፍኝ አሽከር ወይንም የስራቤት አለቃ ማድረግ” ይሻላል። ከዛ ሁሉም ሲስቁ ፊታውራሪም ለጊዜው ይስቁና እብድ እንዳይባል የሚናገረም መርዝ ነው ደህና እንዳይባል እንዲያው አኮ በዲማው…. እስቲ ማን ጠይቆህ ነው ይሄንን ሁሉ የምትዘባርቀው” ይላሉ።
እንደ አባ ሞገሴ ያሉ የእልፍኝ ምሁራኖች በኢትዮጵያ በዝተዋል።
በቄስ ሞገሴ የሚወክሉት የኢትዮጵያ “የእልፍኝ ምሁራን”
እንደ ቄስ ሞገሴ ያሉ ሰዎች በብዙ ልብወለዶች ውስጥ ይገኛሉ። ለምሳሌ የስፓኒሹ በዳን ኪሆቴ “Don Quixote,” መጽሀፍ ውስጥ Don Quixote de la Mancha እናገኛለን። ዳን ኪሆቴ ስሙ ሲሆን ላማንቻ ደግሞ የባላባትነቱ ቦታ ነው። የሱ አሽከር ደግሞ ሳንቾ ፓንዛ (Sancho Panza) ይባላል። ዳን ኪሆቴ አይምሮው የላላና በምናብ አለም ውስጥ ጀግና ለመባል የተነሳ ባላባት ነበር። አሽከሩ ደግሞ ከሱ የባሰ የአለቃውን እብደነትና ጅልነት ተከትሎ አብሮ የዘመተ ነው። ሳንቾ ጌቶች እባኮ ይተዉ፤ ይህ ነገር ግኡዝ ነው ፍጡር አይደለም ማለት እንኳን ይቸገራል። ዳን ኪሆቴ ለመጀመሪያ ግዜ የሚሽከረከር የንፋስ ሀይል (windmill) ሲያይ ይሄንን አውሬ እገላለሁ ብሎ ጎራዴውን መዞ ፈረሱን ኮርኩሮ ሲሸመጥጥ ሳንቾ ፓንዛ የተጫነባትን አህያ ኮርኩሮ እሱም ይከተለዋል። ከዛ የሚሽከረከረው ነገር ዳን ኪሆቴን እና ፈረሱን አስፈንጥሮ ይጥላቸዋል። ከዛ ሳንቾ የአለቃውን አቧራ አራግፎ ወደ ሌላ ስህተት ይከተለዋል።
ታድያ ሳስበው የኛ ሀገር ምሁራኖች እንደነ ቄስ ሞገሴ እና ሳንቾ ፓንዛ ለጌቶቻቸው ፍፁም ተገዢና ምንም ቢሰሩ መገሰፅና ማስተካከል የማይችሉ ሎሌዎች ናቸው። “አረ ይህ ነገር ትክክል አይደለም፤ ስህተት ነው” ብለው ከመገጸስ ይልቅ እንደ አባ ሞገሴ “ጌቶች ያሉት ሁሉ አንድም ስህተት የለው። ሁሉም እውነት ነው። እግዚአብሔር ጌታን ከደሀ፣ ገዢን ከተገዢ ለይቶ ሲሰራ፣ ጌታው ገዢው ፍርድ ቢያጎድልና ደሀ ቢበድል ጠያቂው መንግስት። ከዛም በላይ እግዚአብሄር ነው እንጂ ደሀ አቤት ከማለት አልፎ የሚተደደርበትን ህግን ደንግጎና ፈራጅ ሆኖ አያውቅም። አሁን ባላገር አድሞ የሚሰራው ከጥጋብ በቀር ሌላ ስም የለውም” አሉ ቄስ ሞገሴ።
የገረመኝ ነገር እኚህ በፊታውራሪ መሸሻ አዳራሽ ውስጥ የነበሩት ቄስ ሞገሴ አሁንም ከቤተመንግስት አልወጡም። ወይ እንደ ህንዶቹ ነፍስ ደግመው ደግመው አዲስ ስጋ እየተላበሱ ሳይወለዱ አይቀሩም።
በኮለኔል መንግስቱ ኃይለማርያም እልፍኝ ውስጥ የነ ዶ/ር ገረመው ደበሌ፤ ዶ/ር አሻግሬ ይግለጡ፤ የነ ዶ/ር አለሙ አበበን ስጋ ለብሰው አባ ሞገሴ ነበሩ። አቶ መለስ ቤተመንግስት ሲገቡ ቄስ ሞገሴ የነ ዶ/ር ካሱ ኢላላ፤ የነ ፕሮፌሰር እንድርያስ ስጋ ለብሰው እዛው ቀጠሉ። አሁን ደግሞ ዶ/ር አብይ እልፍኝ ውስጥ የዶ/ር ብርሀኑ ነጋን እና የዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስን ስጋ ለብሰው “ድሮም እግዚአብሔር ጌታን ከደሀ፣ ገዢን ከተገዢ ለይቶ ሲሰራ ሲሉ ይሰማሉ።
ቄስ ሞገሴና ሳንቾ ፓንዛ
ሳንቾ ፓንዛ የልብ ወለድ ገጸ ባህሪ ቢሆንም ብዙ ፈልሳስፋዎች እና የስነልቦና ጠበብቶች የጻፉበት ታዋቂ ጅል ተከታይ ነው። ስለ ታዛዥነት (authority and conformity) ፤ ስለ ጉጉነት፤ ስለ መሪ ተጽዕኖ (Charisma); ስለ እውነታን አለመቀበል (Dissonance: When followers recognize the flaws in their leader but continue to support)፣ ቡድነኝነት ወይንም ብሄረተኝነት (Groupthink)፤ ያለ ጡረታ ማርጀትና ተስፋ ማጣት (Hope and desperation) ምሳሌ ተደርጎ ብዙ ይጠቀሳል። በአጠቃላይ ለመሪ የስነልቦና ባርነት ሲጠቀስ ሳንቾ ይነሳል። የስታሊን ይቅርታ ጠያቂ ተብሎ የሚተቸው አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ዋልተር ዱራንቲ ከነዚህ አይነት ምሁራን ይመደባል ቄስ ሞገሴም አንድ ቀን ኢትዮጵያ ምሁር ካፈራች ወይንም ፈረንጆቹ አማርኛ መናገር ከጀመሩ እንደ ሳንቾ ፓንዛ ፈላስፎች ብዙ ትርጉም እየሰጡ ታዋቂ አድርባይ ያደርጓቸዋል።
እነ ቄስ ሞገሴ እነ ሳንቾ ፓንዛ የገሀዱን አለም ሎሌዎች፤ አሽከሮች እና ታዛዦች ወክለው በምናቡ አለም እንዲጫወቱ የተፈጠሩ ገጸ ባህርያት ናቸው።
ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት እንደ ብርጋዴል ጀነራል አታተርክ (የቱርክ መሪ) ያለ ሰው ነው ሲሉ ያሳፍራል። ዶ/ር ብርሀኑ በመጽሀፋቸው ውስጥ ‘ዲሞክራሲ እንደ አየርና ውሀ ለሰው ልጅ አስፈላጊ ንጥረ ነገር ነው’ ብለው ብዙ ተከታዮች ያፈሩበት ዘመን ነበር። እግዜር ይመስገን እኔ ያኔም አልታለልኩም።
ዶ/ር ብርሀኑ በጻፉት መጽሀፍ ውስጥ ስለ ዲሞክራሲ የህንዱን ኢኮኖሚስት አማርታይ ሴን (Amartya Sen) እየጠቀሱ እንዲህ ጽፈው ነበር። “ነጻነት የእድገት መመዘኛ በመሆኑ ወደ ኢኮኖሚ እድገት ጎዳና የሚደረገው መሻሻል መመለከት የሚቻልበት ዋነኛው መመዘኛ፤ መሻሻሉ የስዎችን የነጻነት አድማስ ምን ያህል አስፍቶታል የሚለው ነው። ……ነጻነት ለእድገት አስፈላጊ መሳሪያ በመሆኑ የኢኮኖሚ እድገት ሊገኝ የሚችለው ነጻ በሆኑ ሰዎች እንቅስቃሴ ወይም ወኪልነት ብቻ ነው”። ……ነጻነትና ዴሞክራሱ ቀስ ብሎ የሚመጣ ነው የሚለው አመለካከት የሚያስኬድ አይደለም። ምክንያቱም በምንም ምክንያት ይህንን የሰው ልጆችን ነጻነት መንፈግ ሆነ ማቆየት የሰውነታቸን ማንነት መንፈግ ወይንም ማቆየት ነው የሚሆነው። …ሰዎችን ሰው የሚያደርጋቸው የነጻነት ፍላጎታቸው በመሆኑ ሆድን እስከምትሞላ ድረስ ነጻነት አያስፈልግም የሚለው አባባል ሰው ሆዱን እስከሚሞላ ሰውነቱን አጥቶ እንደ እንስሣ ይቆጠር የማለት ያህል ነው” (የነጻነት ጎህ ሲቀድ ገጽ 32) ብለው የጻፉት መጽሀፍ ከጃችን አሁንም አለ። አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት እንደ ብርጋዴር ጄኔራል አታተርክ (በኋላ ፊልድ ማርሻል) ያለ አንባገነን ነው ሲሉ ፈገግ አስባሉኝ።
ያኔ “ሰው ያለ ነጻነቱ እንስሳ ሁን ማለት ነው” ሲሉ ብዙ ዶላር ያዋጡ ደጋፊዎቻቸው አሁን እንዴት ይሸማቀቁ። እኔ እንኳን ወደ ቤተመንግስት የሚገቡ “ምሁራኖች” ሁሉ እንደ ቄስ ሞገሴን ፊት አንብበው የሚናገሩ መሆናቸው ቀድሜ በመረዳቴ ምንም አልጠበቅኩም። የእልፍን ምሁራን ይሄንንም ካላደረጉ እንደ በዛብህ በል “የተሰጠህን ጠጣና ውጣ” እንደሚባሉ አውቃለሁ። የኢትዮጵያ ውድቀት ምሁር መፍጠር ያለመቻሏ ነው ብዬ ብዙ ግዜ ጽፌያለሁ።
አታተርክ ማናቸው?
ለማያውቁዋቸው ብርጋዴል ጀነራል አታተርክ ዲሞክራት ሳይሆኑ አንባገነን ነበሩ። የሳቸውን አንባገነንነት በክፍል ሁለት በዝርዝር ተጽፋል። አታተርክ ከስልጣን የወረዱት በዲሞክራሲ ምርጫ ሳይሆን ስልጣን ላይ ሆነው በመሞታቸው ነው። ይሄንን ነው ዶ/ር ብርሀኑ ለኢዜማ ተከታዮቻቸውና ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚመኙለት። የዶ/ር ብርሀኑን ቃለ መጠይቅ “ሰሙና ወርቁን” እናውጣ ካልን። “ሰሙ” አታተርክ ሲሆኑ ወርቁ ደግሞ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት አርጅቶ እሬሳው ከቤተመንግስት የሚወጣ መሪ ነው ለማለት ነው።
ታድያ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ “ሰዎችን ሰው የሚያደርጋቸው የነጻነት ፍላጎታቸው በመሆኑ ሆድን እስከምትሞላ ድረስ ነጻነት አያስፈልግም የሚለው አባባል ሰው ሆዱን እስከሚሞላ ሰውነቱን አጥቶ እንደ እንስሣ ይቆጠር የማለት ያህል ነው” ብለው ጀምረው እንዴት እንደ ቄስ ሞገሴ የሰው ፊት እያዩ አሁን ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት እንደ ጄኔራል አታተርክ ያለ ረግጦ የሚገዛ ወታደር ነው አሉ? ታድያ ቄስ ሞገሴ ለማር ጠጅና ለፊታውራሪ ቁርጥ ብለው ቢያሽቃብጡ ለምን ይፈረድባቸዋል?
ምሁር ማለት የሀሳብ ማምረት ላይ የተሰማራ ማለት እንጂ እነደነ ቄስ ሞገሴ አለቃው ፊት እያየ ሀሳቡን የሚቀያይር የሚያሽቃብጥ ማለት አይደለም። በእርግጥ ጀነራል አታተርክ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ተምሳሌ ከሆን ባለ 500 ገጽ መጽሀፍ ሲጽፉ እንዴት አንድ መስመር እንኳን ነፈጉት? ዶ/ር ብርሃኑ ያልገባቸው ምዕራባውያን ጀነራል አታተርክን ጀግና ጀግና ብለው የጻፉላቸው ተርኪን አዳክመው የምዕራብያውያን አገልጋይ ስላደረጓት ነው። በዚህ ላይ እመለስበታለሁ።
እንደነ ዶ/ር ብርሀኑ ሳያነቡ የሚያምኑትን …. ማን እንበላቸው?
የዶክተር ብርሀኑ ስህተት የመጀመሪያ አይደለም። የዛሬ ሀምሳ ዓመት ዶ/ር ብርሀኑ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሆነው ኮሚኒዝም የሚባል አለም አለ። በዚህ አለም ደግሞ “ሰው ሁሉ የሚችለው ብቻ እሚሰራበትና እንደፍላጎቱ የሚኖርበት” ነውም (“From each according to his ability, to each according to his needs”, Karl Marx)። ይህ ደግሞ እንደ ዛሬው አታተርክ ለኢትዮጵያ ያስፈልጋታል ብለው ምንም ሳይጠይቁ አመኑ ባቻ ሳይሆን ተጋደሉ።
የኢትዮጵያ 80 በመቶ በላይ የሚሆነው ትውልድ ከሶሻሊዝም መፍረስ በኋላ የተወለደ ስለሆነ ይህንን የነ ዶ/ር ብርሀኑን መሪ ቃል እስቲ በቀላል በምሳሌ እንተንትነው።
እነ ዶ/ር ብርሀኑ እንፈጥረዋለን ብለው የሸፈቱለት መሪህ ቃል የአንድ ሰው ችሎታው የጥበቃ ስራ ቢሆን ፍላጎቱ ደግሞ ሸራተን ውስጥ መኖር ቢሆን መብቱ ነው የሚል ነው። ይህ ጥበቃ ከስራ ሲወጣ ጀርባውን ሸራተን ሄዶ ታሽቶ፤ ዋኝቶ፤ አራት ተከታይ ያለው እራቱን በልቶ፤ ትንሽ ኮኛክ ተጎንጭቶ፣ በቱጃሩ በአቶ አላሙዲ መኝታ ላይ ጧ ብሎ የሚተኛበት ስርአት ለመፍጠር ነው ዶ/ር ብርሀኑ ጠመንጃ አንስተው ጫካ የገቡት። ይህ ጥበቃው ጥዋት ሲነሳ “እድሜ ለካርል ማርክስ” ብሎ ቁርሱን በልቶ ወደ ጥበቃ ስራው የመሄድ አለም እንፈጥራለን ብለው ነበር። የዚህ ምኞት ክፋቱ ይህ ጥበቃ ሸራተን የሚተኛው አነ ጸሀፊ ትዕዛዝ አክሊሉን፤ እነ ልጅ አንዳርካቸው መኮንን፤ እነ ቀዳማዊ ኃይለስላሴን ከገደለ ብቻ ነው።
መቼም እንኳን ዩኒቨርስቲ የገባ ሰው የፊታውራሪ ባላገሮችም ቢሆኑ አንድ ሰው ከሚያመርተው በላይ የሚመገብ ከሆነ ይሄንን ትርፍ ፍጆታ የሚያመርት ሌላ ሰው መኖር አለበት ። ይሄንን መጠየቅ የሚያስችል አይምሮ አልነበራቸውምን? ትርፍ ፍጆታ ለሌላው የሚያመርት ካለ ደግሞ ይህ አምራች ወይ ባርያ አለበለዚያም የሚበዘበዘ ወዛደር ነው ማለት አይደለምን?
ሁለተኛው ጥፋት፡ እነ ዶ/ር ብርሀኑ ቪቫ መንግስቱ
ኤልያስ ተባባል ?ገንዘብ አላት ብሎ መልከ ጥፉ ማግባት፣ ገንዘቧም ያልቅና ሁለተኛው ጥፋት” ያለው ደግሞ የነ ዶ/ር ብርሀኑና የሻለቃ መንግስቱ ፍቅር ነው። አዲሱ ትውልድ ይሄንን አያውቅም።
እነ ዶ/ር ብርሀኑ በእድገት በህብረት ዘመቻ ሰልፍ ላይ መንግስቱ ከሶስቱ መሪዎች ተነጥሎ ጨካኝ በመሆኑና የቀድሞ አርበኞችን ይረሽናል ስለተባለ እነ ጀነራል ተፈሪ በንቲ ደግሞ ትንሽ አይምሮ ስላላቸው እነ ጀነራል ተፈሪ በንቲን ቆመው እነ ዶ/ር ብርሀኑ “ቪቫ መንግስቱ!!” ሲሉት ዋሉ። ቪቫ መንግስቱ ወዲያው ጠመንጃቸውን ወደነ ብርሀኑ ነጋ ላይ ሲያዞሩ መንግስቱ ፋሽስቱ አሉ። አስቀድሞ ነበር መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ ሆነ ነገሩ። ልክ እነ ዶ/ር ሀይሌ ፊዳ ለሻለቃ መንግስቱ የእልፍኝ ምሁር ሆነው ቀይ ሽብር እንዳወጁት ሁሉ ዛሬም ዶ/ር ብርሀኑ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት እንደ ፊልድ ማርሻል አታተርክ ያለ ባለ ጅራፉ ነው አሉ። አንድ ቀን ከእንቅልፋቸው ሲነቁ አንድ ሚሊዮን ሰው ታርዶ እጃቸው በደም ተጨማልቆ ያገኙታል።
ታድያ ትላንት የሰው ጥረትና የሰው ፍላጎት የተፋታበት ስርአት ይኖራል ብለው አስበው ገድለው የቁልቁለት መንገዱን የቀደዱ ዶ/ር ብርሀኑ ዛሬ ደግሞ ካልጠፋ ሰው ለኢትዮጵያውያን የሚያስፈልጋቸው በጅራፍ ወታደራዊ አንባገነንነት ነው ይላሉ።
የእልፍኝ ምሁራን ሁሌም አለቆቻቸውን ለማስደሰት ብለው የሚቀባጥሩት ሁሌም ለራሳቸው ይተርፋል። ቄስ ሞገሴም በፊታውራሪ እርሶ በማያውቁት ገብተው አይዘባርቁ ይባላሉ። ከታሪክ ከተማርን እነ ዶ/ር ሀይሌ ፊዳም ፒኤች ዲም ቢኖራቸውም እነ ሻለቃ መንግስቱ፤ እነ ደበላ ዲንሳ እና እነ ሀምሳ አለቃ ለገሰ አስፋው ትምህርቱን ወስደው አስተማሪዎቹን ለቁርስ ነው ያቀረቡዋቸው።
ፈረንጆቹ የምትሳለውን በደንብ እወቅ፤ ምኞትህ ይደርስና እንዳትቸገር ይላሉ። የኢትዮጵያ “ተራማጅ” ተማሪዎች ወዛደራዊ አንባገነንነትን ተመኙ ወዲያው ወታደራዊ አንባገነንነትን ተሰጣቸው። ያው ወታደርስ የወዝና የደም አደር አይደል።
መለስ ብለን ስናየው እነ ዶ/ር ብርሀኑ እንደነ ሳንቾ ፓንዛ እንዲህ አይነት አለም አለ ብለው ማመናቸው ችግር አልነበረው። ችግሩ ይሄንን አለም ለማምጣት የኢትዮጵያን አርበኞች፣ ንጉሱ ነገስቱን፣ ጳጳሱን እና አባቶቻቸውን አደሀሪ ብሎ መግረፍና መግደላቸው ነው።
የዛሬ 50 አመት ለዚህ ሀገር ደማቸውንን የሰጡና የሞሶሎኒን ስርአት የመከቱ ኢትዮጵያውያንን አርበኞች እነ ጸሀፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀበተወልድን፤ እነ ራስ መስፍን ስለሺን፤ እነ አማን አምዶምን ረሸኑ።
ሶስተኛው ጥፋት ያንኪ ጎ ሆም
ይሄንን ጭፍጨፋ ሲጨርሱ ጠመንጃው ወደነ ዶ/ር ብርሀኑ ሲዞር እነ ዶ/ር ብርሀኑ ወደ ተመኙት ሰሜን ኮርያ፤ ኪዩባ፤ ሩስያ ወይንም ሶሻሊስት ቻይና አይደለም የተሰደዱት። የሚያስቀው የተሰደዱት ያ ኢንፔርያሊዝም የወረቀት ነብር ነው! ኢንፔሪያሊዝም ይወድማል! አንጠራጠርም የታሪክ ሀቅ ነው! ያንኪ ጎ ሆም! (Yankee Go Home!!) ብለው ወደ አወገዙት የኢንፔሪያሊስ ሀገር ነው። አዲስ አባባ ላይ አሜሪካውያን ከሀገራቸን ውጡ ብለው ቀውጢ ሲያደርጉ የነበሩ እነ ዶ/ር ብርሁኑ አሜሪካኖቹን ቀድመው አሜሪካ ገቡ። እንዲህ አይነት ህሊና የሌላቸው ሰዎች በአለማችን ይኖሩ ይሆን? እስቲ እግዚአብሄር ያሳያችሁ እዚህ አዲስ አበባ ላይ አሜሪካኖች ከሀገራችን ውጡ (Yankee Go Home!!) ብሎ የተሳደበና ያባረረ አይኑን በጨው አጥቦ አሜሪካ ጥገኝነት ይጠይቃል?
ይሄንን የማነሳው የነ ዶ/ር ብርሀኑ ትምህርት ለማመዛዘን ሳይሆን ለቆብ ብቻ መሆኑን ለማሳየት ነው። ደርግ ግራዝማች፤ ባላንባራስ፤ ቢተወደድ፤ ደጃዝማች፣ በጅሮንድ ወዘተ የሚለውን ለዘመናት የቆየ ማዕረግ ስላገደ ዛሬ ሰው የሚማረው አቶ ላለመባል እንጂ በሀሳብ ምርት ሞያ ላይ ለመሰማራት አይደለም።
ዶክተር እንደ ግራዝማችነት
በአለም ላይ ብዙ ባለ ፒኤች ዲ ያላቸው የሀገር መሪዎች አሉ ግን ከማስተማርና ከምርምር ሲወጡ ወደ ፓለቲካ ሲገቡ ዶክተር ተብለው አይጠሩም። ዶ/ር የምርምርና የማስተማር ሞያ ማዕረግ ነው።
ዛሬ ጉግል ብናደርግ ዶክትሬት ያላቸው ግን ዶክተር ተብለው የማይጠሩበት መሪዎች ብዙ ናቸው። ለምሳሌ የሩሲያው መሪ ፑቱን በኢኮኖሚክስ ፒኤች ዲ ዲግሪ አላቸው ግን ዶክተር ፑቲን ሲባሉ አልሰማንም። የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የህግ ፒኤች ዲ (Juris Doctor (JD) አላቸው ይሁንና ዶክተር ባይደን ሲባሉ አልሰማሁም፤ የጀርመኑዋ አንጄላ መርክል በኬሚስትሪ ፒኤች ዲ አላቸው፤ የህንዱ ማንሞሃን ሲንግ (Manmohan Singh)፤ የቻይናው ዜንፒንግ (Xi Jinping)፤ የእንግሊዝ ባለፈው የወረዱት ሱናክ (Rishi Sunak) ከኦክስፎርድ የኢኮኖሚክስ ፒኤች ዲ አላቸው። የአሁኑ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስቴር የሆኑት ስታርመር (Keir Starmer) የህግ ፒኤች ዲ አላቸው። የቀድሞውም የእንግሊዝ መሪ ጎርደን ብራወን የታሪክ ዶክተሬት አላቸው። ግን ማናቸውም ዶ/ር ሱናክ፤ ዶ/ር ፑቲን፤ ዶ/ር ባይደን ተብለው አይጠሩም። እኛ ሀገር ግን ቀኛዝማችና ባላንባራስ ማንጠልጠያው ስለታገደ ዶ/ር እንደ ባላንባራስነት ማንጠልጠያ ሆነ እንጂ ለማሰብያ ለማሰላሰያ ሲውል አይታይም። ዶ/ር ብርሀኑ ለ20 ዓመታት ጋዜጣ ላይ እንኳን ስለ ኢኮኖሚ፤ ዋጋ ግሽበት፤ የገንዘብ ግሽበት እንኳን አስተያየት ጽፈው አላየሁም። አንድ ዲግሪ ለአምስት አመት ካልተጠቀሙበት አንድ ሰው የተማረው ነገር ሁሉ ጊዜ ያልፍበታል ይባላል።
አንድ ሰው ፒኤች ዲ (PhD) የሚማረው በሀሳብ ማምረት ስራ ላይ ለመሰማራት ብቻ ነው። “ምሁር” የሚለው ትክክለኛ ትርጉሙ ሞያው ሀሳብ ማመንጨት ብቻ የሆነ ማለት ነው ይላል ቶማስ ስዌል / Tomas Swell በ Intellectuals and society በሚለው መጽሀፉ። (Intellectual’s work begins and ends with ideas} “intellectuals” refers to an occupational category, people whose occupations deal primarily with ideas—writers, academics, and the like. Most of us do not think of brain surgeons or engineers as intellectuals, despite the demanding mental training that each goes through and despite the intellectual challenges of their occupations. Similarly, virtually no one regards even the most brilliant and successful financial wizard as an intellectual)
ዶ/ር ብርሀኑ መቼም በሀሳብ ምርት ላይ ተሰማርተው ያፈራና የታጨደ ምንም ምርት አላሳዩንም። እነ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ የዛሬ መቶ አመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምን ይምሰል ብለው ጽፈው ሞቱ። አሁን ከዶክተርነቱ በቀር ቄሱም ዝም መጽሀፉም ዝም ሆንዋል።
መደምደሚያ አቋም ማጣት?
ከላይ እንዳየነው ዶ/ር ብርሀኑ ብዙ ግዜ ሳያስቡ የሚናገሩ ይመስለኛል ወይንም ስህተት ይወዳቸዋል። እሳቸው አንዴ በቁምጣ አንዴ ቦላሌ ሱሪ ሲታጠቁ ነው እድሜያቸውን የፈጁት። አንድ ቀን “ፋኖ ተሰማራ እንደ ሆቹ ሚኒ አንደ ቼኩቬራ”፤ በሁለተኛው ቀን “የማይቀለበሰው የሰላማዊ ትግል”፤ ካዛ በሶስተኛው ቀን ካኪ ለብሰው “ወያኔን በሚያውቀው ቋንቋ እናንቆራጥጠዋለን” በአራተኛው ቀን ደግሞ ጠመንጃ ያነሱ “ወንበዴዎች ናቸው” ሲሉ ይሰማሉ። ይሁንና በህይወታቸአ አስመዘገብኩ የሚሉት ድል ግን የለም። ማሸነፍ ማሰብ ይጠይቃል። በመታጠቅ በመፍታት ድል አይመጣም። ስህተት በጣም ይወዳቸዋል። አንድ ቀን ዲሞክራሲ ለህዝብ አየር ነው በማግስቱ ደግሞ እንደ ጀነራል አታተርክ ያለ መሪ ነው ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ይላሉ።
ምሁርነት የውሀ ላይ ኩበት ከሆነ ሳንቾ ፓንዛና ቄስ ሞገሴ በስንት ጣእማቸው። ሰው ሳይገሉ ሳይታጠቁ ሳይፈቱ ያሳስቁናል። በክፍል ሁለት አታተርክ ምን ሰሩ የሚለውን እመጣለሁ።
መልካም ሳምንት