ታህሣሥ ፲፪ ቀን ፳፻፲፮ ዓ/ም
ከኢያሱ ዘአዲስ አበባ
የአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል በድል ላይ ድል እያስመዘገበ ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረ የሚገኝ እንደመሆኑ ውጤታማነቱን ለማስጠበቅና የህልውና ትግሉ ግቡን እስኪመታ ድረስ ለማዝለቅ፣ ትግሉ የሚገኝበትን ደረጃና ሂደት በመገምገምና ትግሉ ያስገኘውን በጎ ዕድል በመተንተን፣ የታዩ ድክመቶችንና ስጋቶችን ከግምት በማስገባት ሊወሰዱ የሚገባቸውን ቀጣይ እርምጃዎች በሚከተሉት ነጥቦች ለመጠቆም ተሞክሯል፡፡
ትግሉ የሚገኝበት አዎንታዊ ደረጃና ሂደት
- አብዛኛው የአማራ ሕዝብ የብልጽግናን መንግሥት፣ በተለይ ወላጆቹን ሕወሐትንና ኦነግን፣ እንዲሁም ማንኛውም በዘረኝነት ላይ የተመሠረተን የፖለቲካ ርእዮት የሚያራምድ አካል ፀረ-ዐማራ፥ ፀረ ነባር ባህልና እምነት፥ ፀረ-ኢትዮጵያ መሆኑን፤ ይህም ሁኔታ ከኢትዮጵያ የነፃነት ጠላቶች ሤራ የመነጨ እንደሆነ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።
- የአማራና የኢትዮጵያ ህልውና የሚረጋገጠው አሁን በአገራችን የተንሠራፋው በዘር ላይ የተመሠረተው ወገንተኛ የፖለቲካ ዘይቤና ተቋማት፥ ሕጎች፥ ትርክቶችና ትምህርቶች ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተሸንፈው ሲጠፉ እንደሆነ የተገነዘቡ የአማራ ምሁራንና ወጣቶች ቁጥር ከፍተኛ ሆኗል።
- የአማራ ሕዝብ የህልውና ተጋድሎ በመዋቅር ደረጃ፣ በፋኖ ኃይሎች ያልተማከለና ከፊል የተማከለ ሆኖ በነፃነት የአካባቢን ሁኔታ እያገናዘበ የሚንቀሳቀስ ፈጣን አሠራር ያለው ከመሆኑ ባሻገር በመርሕና በእሤት፥ በግብና በአካሄድ ደረጃ ፍጹም የተስማማ (የተማከለ አመራር) ያለው ሆኖ በጦር ሜዳ ተጋድሎ በድል ላይ ድል እያስመዘገበ ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን አረጋግጧል።
- “አዲሲቷ” ኢትዮጵያ ለተባለች እና በነባር ሕዝቦች ባህል፥ እምነት፥ ተፈጥሮአዊ ህልውናና የማኅበረሰብ መዋቅር መቃብር ላይ ለምትመሠረት አገር ወይንም ለታላቋ የትግራይ ሪፐብሊክና ለታላቋ የምሥራቅ አፍሪቃ ገዥ ኦሮሚያ መመሥረት መደላድል የሆነው የሕወሐትና የኦነግ ጥምር ፕሮጄክት ማስፈጸሚያ የዘር ሕገ መንግሥት መሆኑን አማራ በተለይ እና ሌሎች ማኅበረሰቦች እንደሚገባ ተረድተውታል፥ ሤራውም ተጋልጧል።
- የብልጽግና መንግሥት (ኦነግ/ኦሮሙማ) ፍልስፍና የሆነው ፖለቲካዊ ኦሮሙማ፣ የኢትዮጵያዊነትን መሠረቶችና ህዝቦቿን በማጥፋት በምሥራቅ አፍሪካ አዲስ ታላቅ የአፓርታይድ መንግሥት ለመመሥረት አስቀድሞ አማራንና ኦርቶዶክስን ማጥፋት እና ቀጥሎ ሌሎች ማኅበረሰቦችን በመጨፍለቅ እንደሚተገበር ግብ እንዳደረገ በተግባሮቹ ሳይሸፋፈንና ለማስተባበል በማይቻልበት ደረጃ ሱማሌን፥ አፋርን፥ ሲዳማን፥ ኮንሶን፥ ጋሞን፥ ጉራጌን ወዘተ ለማጥፋትና ለመዋጥ በሚያደርገው ጥረት ተጋልጧል።
- የአማራ ሕዝብ የህልውና ተጋድሎ፣ ከራሱ አልፎ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ሌሎች ብሔረሰቦችን ለመታደግ፤ ዓይኑን አፍጥጦ ጥርሱን አግጥጦ ሊያጠፋ ከመጣው ከኅሊና ቢሱ ፖለቲካዊ ኦሮሙማ የመዳን ተስፋ ፈንጥቋል።
- የአማራ ሕዝብና በፋኖነት የተደራጀው ተዋጊ፣ ለልጆቹ ነፃ አውጭና መፍትሔ ሰጭ ሁለተኛ ወገን እየተጠባበቀ በባሪያ ስነ ልቦና ታሥሮ ከአንደኛው ባርነት ወደ አዲስ ሌላ ከፋፍሎ ወደሚገዛ ነፃ አውጭ-ነኝ-ባይ-ገዥ ሲሸጋገር 50 ዓመታትን ያስቆጠረውን ማኅበረሰብ ከዚህ ክፉ ልማድ የሚያላቅቅ ራስን በራስ መሥዋዕትነት የማዳን ነባሩን ኢትዮጵያዊ መንገድ መልሶ አነቃቅቶታል።
ትግሉ ያስገኘው በጎ ዕድል
- በዘር ላይ የተመሠረተው የብልጽግና መንግሥት የሕዝብ ጠላትነት ግልጽ መውጣቱ፣ ለአማራ ሕዝብ ከማመንታት መውጣትና በሙሉ ልብ ወደ ትግል የመግባት እድል መፍጠሩ።
- የብልጽግና መንግሥት ፖለቲካዊ ኦሮሙማ ርእዮት፡ የሃይማኖት፥ የባህልና የተፈጥሮ የማኅበረሰብ ብዝኃነት ጠላትነቱን በግልጽ እና በተግባር መግለጡ፣ ዒላማ የተደረጉ ማኅበረሰቦችን ሁሉ ለማስተባበር እድል መፍጠሩ።
- የአማራ ሕዝብ የትጥቅ ተጋድሎ የበላይነት ከጦርነቱ ፍትሐዊነት፥ ከባህላዊ ጀግንነትና አማራጭ የሚያሳጣ ጠላት መከሰት ጋር ተደምሮ አሸናፊ እየሆነ መምጣት።
- የፖለቲካዊ ኦሮሙማ ርእዮት ከፀረ ኢትዮጵያዊነት አልፎ ለምሥራቅ አፍሪካ ውህደትና ለፓን አፍሪካዊ ሂደት እንቅፋት መሆኑን በማጋላጥ ቀጠናውንና አህጉሩን በሥርዓቱ ላይ የማስተባበር እድል መኖሩ።
- የኦነግ ፖለቲካዊ የብልጽግና ኦሮሙማና የሕወሐት ፀረ ኢትዮጵያና ፀረ አማራ አቋሞችን የተረዱ ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰቦችን የማስተባበር እድል መክፈቱ።
- የኤርትራ መንግሥት ለአማራ የህልውና ተጋድሎ አዎንታዊ ምልከታ ማሳየት።
የትግሉ ውስጣዊ እንቅፋቶች
- የግል ሥልጣን፥ ዝናና ጥቅም የሚፈልጉ፥ ሰፊ ኔትዎርክና የቀደመ ዝና ያላቸው ግለሰቦች ራሳቸውን ለማንገሥ ትግሉን በፕሮፓጋንዳና በሤራ ለራሳቸው ተጠሪ የማድረግ ሙከራዎች የሚፈጥረው የእርስ በርስ ጥርጣሬ ወይም እኔም ከማን አንሳለሁ የሚል ስነ ልቦና የመፈጠር እድል መኖሩ።
- በውጭና በአገር ውስጥ ትግሉን በሐሳብና በሀብት ለመደገፍ የሚሰባሰቡ ተዋንያን የሚመሩበት የጋራ የሂደት፥ የኮሚዩኒኬሽን፥ የዲፕሎማሲ፣ የድጋፍ አሰጣጥና የሚዲያ አጠቃቀም የጋራ መርሕ አለመፍጠር።
- የሚዲያ ባለሙያዎች ከሚናቸው ውጭ ትግሉን በመሰላቸው መንገድ አቅጣጫ የመስጠት፥ የወደዱትን መሪ የመካብና ያልወደዱትን የማጠልሸት ሂደት፥ ስልክ እየደወሉና መልእክት እየላኩ የመከፋፈል ክፉ ልማድ።
- በገንዘብና በሥልጣን የሚደለሉ የሚሊሻ፥ የፖሊስና የንዑስ ማንነት ፖለቲካ አራማጅ ልሂቃን ለአገዛዙ በመረጃ አቀባይነትና በአስጠቂነት ማገልገል።
- የተወሰኑ ሰዎችና ቡድኖችን በቀደመ የትግል ተሳትፎአቸው “ጠላት” አድርጎ በመፈረጅ የተጋድሎ ጎራውን መከፋፈልና ማሳሳት።
- የአማራን ተጋድሎ ከኦርቶዶክስ ሃይማኖት ጋር የማቆራኘት ወይም የመነጠል ፕሮፓጋንዳና አስተሳሰብን በግልጽ የማስታረቁ እና ሌሎች እምነቶችንና ባህሎችን የማካተቱ ተቃርኖ ግልጽ አለመሆኑን የሚጠቀሙ ከፋፋዮች መኖራቸው።
የትግሉ ውጫዊ እንቅፋቶችና የጠላት የማጥቃት ስልት
- ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የመሠረቱ ነባር እምነቶችና ባህሎችን በማጥፋት አዲስ የብሔረሰብ ሪፐብሊክ ለመፍጠር 50 ዓመታት የደከሙት የሕወሐትና የኦነግ ድቅል የሆነው የብልጽግና መንግሥት ለግቡ መሳካት ይረዳው ዘንድ አማራን፣ ኦርቶዶክስንና ነባሩን እስልምና ለማጥፋት የቀየሰው ስልት፦
- ሕወሐት ሲያደርገው እንደኖረው፣ በአማራ ክልል የሚኖሩ ንዑሳን ማንነቶችን (የቅማንት ኮሚቴ፥ የአገው ሸንጎ፥ የከሚሴ ኦነግ፥ የጉምዝ ነፃ አውጭ) ከአማራ አካልነት ነጥሎ ማሳመፅና ግጭት መፍጠር፤
- የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ሲኖዶስ በጎሳ መከፋፈል፤
- በአማራና በትግራይ፥ በአማራና በኦሮሞ (ሸዋ፥ ወለጋ) ማኅበረሰቦች መካከል ግጭትና አለመተማመንን ማስቀጠል፤
- ነባሩን እስልምና በማጥፋት በአክራሪው እስልምና የመተካት ሂደት፤
- አማራን በማስራብ፥ በበሽታ እንዲጠቃ በማድረግ፥ በአካባቢው ልማት እንዳይኖርና ተዘዋውሮ እንዳይሠራ በማሰነካከል ማዳከም፤
- ሕዝቡን በጦርነት መፍጀት፤
- አማራን ከሌሎች የአገራችን ክልሎች ማጽዳት ናቸው፡፡
- የአንዳንድ የውጭ አገራት ከኦነግ/ኦሮሙማና ከሕወሐት ጋር በመቆም በኦርቶዶክስና በአማራ ላይ የሚደረገውን ዘር የማጥፋት ፕሮጄክት በዝምታ ከመታዘብ እስከ መደገፍ አቋም መያዝ።
- የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ሌሎች ሕዝቦችንና ኦሮሞ ቢሆኑም ኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖታቸውን፥ ነባር እስልምናቸውን፥ ኢትዮጵያዊነታቸውን ያፀኑ ወገኖችን በተለያዩ ኢመደበኛ አደረጃጀቶች የማጽዳት ስልቱን አጠናክሮ መቀጠል።
- በብልጽግና መንግሥት ጋባዥነት፣ የአማራን፥ የጋምቤላንና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎችን በሱዳን ማስወረር።
- የአልሸባብ ከውስጥ ጽንፈኞች ጋር ትይይዝ መፍጠርና በእምነቶች መካከል ተጨማሪ ችግር የመፍጠር እድል።
- አማራን፣ ኦርቶዶክስንና ነባሩን እስልምና አጥፍቶ የብሔረሰብ ሪፐብሊክ የመፍጠር ፕሮጄክታቸውን ለማሳለጥ፣ የኦነግና የሕወሐት እርስ በርሳቸውና ከውጭ አገራት የቀይ ባሕርና የአባይ ወንዝ ጂኦፖለቲካዊ ተዋንያን ጋር ተባብረው አማራንና ሌሎች የኢትዮጵያ ኃይሎችን በቀጥታና በተዘዋዋሪ ማዳከም።
- በብልጽግናና በሕወሐት የሚፈጸሙ የደቡብ ሕዝቦችን፥ ሶማሌንና አፋርን የማጋጨትና የማዳከም፥ ከአማራ ትግል ጋር እንዳይተባበሩ ፋታ የመንሳትና ጥርጣሬ የመዝራት ጥረቶችን የሚመለከታቸው ሕዝቦች ተረድተው የመከላከል ጥንካሬና አንድነትን አለመገንባት።
እንቅፋቶችን የማስወገድ አስፈላጊ እርምጃዎች
- ለግል ሥልጣን፥ ለግል ዝናና ለቡድን ጥቅም በመቆም የአማራን የህልውና ትግል ለመምራት የሚሞክሩ ግለሰቦችና ቡድኖችን በትክክል ለይቶ አደብ ማስገዛት።
- ትግሉን ለመደገፍ በውስጥና በውጭ አገራት በመደራጀትም ይሁን በግል የሚንቀሳቀሱ አካላት የሚመሩበትን ሥርዓት፥ መርሕና የግንኙነት መሥመር ግልጽ በማድረግ ከዚያ ውጭ የሆነውን ሁሉ ከትግሉ መሥመር ቆርጦ መጣል።
- በአማራ ክልል ሕዝብን ለመከፋፈል መሣሪያ የሆኑ የውስጥ ባንዳዎችን በዝርዝር ለይቶ መከታተል።
- በጎሳ ፖለቲካ፥ በማርክሳዊ አብዮት/አመፅ የተሳተፉ ሤረኞች፥ ጓዶቻቸውን በመካድ ራሳቸውን ሲያገለግሉ የኖሩ ሰዎች ወደ አማራ የህልውና ትግል እንዳይቀላቀሉ በጥንቃቄ ለይቶ መከላከል።
- በገንዘብ፥ በሥልጣንና በልዩ ልዩ መደለያዎች የባንዳነትና የስለላ ሥራ የሚሠሩ ሰዎችን በጥንቃቄ ለይቶ አደብ ማስገዛት።
- አማራነትን ከአገራዊና ከህልውና ትግል በማሳነስ እንደ ኦነግና ሕወሐት የጠባብ ብሔረሰብ ልዩ ጥቅም፥ ዘረፋ፥ የበላይነት እና ሥልጣንን በመጠቅለል በሌሎች የበታችነት ለመንገሥ የሚደረግ ትግል አስመስለው ሕዝብን ግራ ከሚያጋቡ የጠላት ፕሮፓጋንዳዎች ለመከላከል የሚያስችል ግልጽ ግብ፥ መርሕ፥ የፖለቲካና የአስተዳደር ዕሳቤ ለሕዝቡ መግለጽ።
- ከአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል በድል መጠናቀቅ ቀጥሎ የዜጎችን እኩልነት፥ የአገር ሙሉ ባለቤትነት፥ የፍትሕ መስፈንና ሰብአዊ ክብር መረጋገጥ፥ የበዳዮች በሕግ መጠየቅና የተበዳዮች መካስ ጉዳይ ምን መምሰል እንደሚገባው ከወዲሁ መጠነኛ ፍንጭ በማሳየት የታፈኑ ወገኖች ሁሉ ትግሉን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ማቅረብ።
- የአማራ ሕዝባዊ የህልውና ተጋድሎን ፍኖተ ካርታ ከትጥቅ ትግል ማብቂያና የመንግሥት ምሥረታ፥ ከዘለቄታዊ የሕዝብ ሙሉ የአገር ባለቤትነትና እኩልነት፥ የዘረኝነት ፖለቲካ ከአገራችን ተጠራርጎ መወገድና የሕዝቦች ነፃ እንቅስቃሴና ነፃ ውሕደት፥ የአገር ሉዓላዊነት፥ የዘመናት ግፎችን በሚመለከት ስለሚኖረው የፍትሕ አሰጣጥና የተበዳዮች መካስ፥ ስለ መንግሥት ቅርፅና የመጭው ዘመን ተስፋን በተመለከተ እንደ ቁማርተኞቹ ፖለቲከኞች ለፕሮፓጋንዳ ሳይሆን በእውነትና በተግባር የሚፈጸመውን መጠቆም ተገቢ ነው።