የፋኖ አንድነት ምክር ቤት ምሥረታን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተሰጠ መግለጫ

ክፍል 1
ስለ ፋኖ ሁሉም ሊያውቀው የሚገባ እውነታ
መግቢያ
ፋኖ በዩቲዩብና በአንዳንድ ሚዲያዎች እንደሚነገረው ‘አንድ ያልሆነ፣ አንድ አመራርና ቅንጅት የሌለው፣ ”በጥይት ቅንድብ የሚላጭ” ነገር ግን ብዙ የሚያስብ ሰው የሌለበት፣ ማኒፌስቶ ያልጻፈና ወዴት መድረስ እንዳለበት በቅጡ የማያውቅ ተደርጎ ሲሳል እናያለን። እነዚህ እውነት ናቸውን? ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ እንዲሉ የፋኖ አንድነት ምክር ቤት የራሱን ድህረ ገጽና ዩቲዩብ አቋቁማል። ከባለቤቱና ከመስክ ላይ የተዘጋጀውን ጽሁፍ በትዕግስት ላነበበ እውነታውን ይረዳል፤ ጥያቄዎቹም ይመለሳሉ።
እውነት ለመናገር ከሆነ በየትኛውም መመዘኛ ከታየ ባለፉት 70 ዓመታት ከተቋቋሙ “የነጻነት ታጋዮች” ነን ከሚሉ ቡድኖች በላይ ፋኖ አንድ የሆነና ምሉዕ የሆነ ድርጅት ነው። ጀበሀን፣ ሻዕቢያን፣ ህወሓትን እና ኦነግን እንደ ምሳሌ ካየን አንድ ሺ ተዋጊ ላይ ለመድረስ ከአስር ዓመታት በላይ ነበር የፈጀባቸው። ህወሓትም በሻዕቢያ ሜካናይዝድ ታግዞ አዲስ አበባ ሲገባ፣ የነበረው ጦር 60ሺ ነበር።
ሁሉም ነፃ አውጪ ነን ባዮች ከግባቸው ለመድረስ የተነሱት በባእዳን የፖለቲካ ዕሳቤ ላይ ተመሥርተውና በአገራቸው ውስጥ “አንዱን ጠላትና አንዱን ወዳጅ” በማድረግ፥ አንዱን ዝቅ ሌላውን ከፍ በማድረግ ነበር። እምነቶችን ሳይቀር አንዱን የጠላት ሌላውን የወዳጅ ብለው በመፈረጅ ነበር። የፋኖ መከሰት እንደ ቀደሙት ንቅናቄዎች የውጭ ጠላት የመከረው፥ የባእዳን አስተሳሰብ አእምሮውን የተቆጣጠረው፥ የሕዝብን ዕሴት፣ ታሪክ፣ አስተዳደር፣ የፍትሕ ሥርዓት፥ ሃይማኖትና ባህልን በመቃረን በጥቂት ልሂቃን ስብሰባ የተወለደ አይደለም። በተፈጥሮ የሚገኝ ራስን ከጥፋት የመከላከል፥ ከፍ ሲል ደግሞ ታሪክን፥ የሕዝብን ልዕልና፥ የአገርን ሉዓላዊነት ከጎሣ ልሂቃን እብደት ለመከላከል የተወለደ ሰዋዊና ኢትዮጵያዊ ነው።
ይህን ተፈጥሮአዊ የህልውና መጠበቅ ማኅበራዊና አገራዊ ግዴታ ለመወጣት በየቦታው ቢያንስ ለአራት ዓመታት በህቡዕ ሲደራጁ፥ ሲማማሩ፥ ሲሰለጥኑ የቆዩ የማኅበረሰቡ ልጆች ናቸው የዘር ማጥፋቱ ፕሮጄክት ከሁሉም አቅጣጫ በግልጽ ሲጀመር ወደ አንድነት የመጡት። ወያኔና ብልጽግና በፈጠሩት ግብግብ ዳፋው ወደ አማራና አፋር ተሸጋግሮ ወደ እልቂትና የመሠረተ ልማት ውድመት በመፋጠኑ፣ አቅዶት ከነበረው ጊዜ ቀደም ብሎ ከተደበቀበት ህቡዕነት ራሱን ለመከላከል ይፋ ሆኖ ወጣ።

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በመቀስቀሱና “ፎጣ ለባሹን እቀጣዋለሁ”፤ የምናወራርደው ሒሳብ አለን፥ የምኒልክና የዮሐንስን ልጆች አጋጭተን ዝሆንነታችንን እናረጋግጣለን፥ በአማራ መቃብር ላይ አዲሲቷን ኢትዮጵያ እንገነባለን የሚሉ ኃይሎች ወደ ክልሉ ስለገቡ ፋኖ የአማራን ህዝብ ከመጥፋትና ሊጫንበት ከታቀደው የባርነት ቀንበር ለመከላከል ህዝቡ ቀድሞ በህቡዕ ሲሠራ ለነበረው ኃይል አቅም ለመሆን በራሱ ከታች ወደ ላይ መደራጀትና ስልጠና መውሰድ ጀመረ። ከእነዚህ በቅድሚያ ከተሰባሰቡትና አዲስ እየተፈጠሩ ከመጡት መካከል በግልጽ አደረጃጀት የየራሳቸውን መሪዎች አበጅተው ከሚንቀሳቀሱት መካከል አብዛኛዎቹ መሪዎች የተወከሉበት “የአማራ ፋኖ አንድነት ምክር ቤት” ተመሠረተ።
“በአማራ ፋኖ አንድነት ምክር ቤት” ሥር የተሰባሰቡት ብርጌዶች በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ 55 ሺ ሰራዊት ገነቡ። መንግሥት በግልጽ በአማራ ሕዝብ ላይ ጦርነት አውጆ ሠራዊት በማዝመት፥ የግብርና ግብዓት በመንፈግ፥ ወደ አዲስ አበባ መግባትን በመከልከል፥ የህክምና መድኀኒቶችን በመንፈግና፣ ተረጂዎችን በማስራብ፥ የመገናኛ አውታሮችን በመቁረጥ፣ ገዳማትን ሳይቀር በመድፍ መደብደብ ጀመረ። ፋኖ በዛ ጊዜ አማራጩ ስለጠበበ ወደ ጫካ ገብቶ፣ አካባቢውን ተለማምዶ፣ ወታደራዊ አሰላለፉን አስተካክሎ፣ እቅድ አውጥቶ፣ ከሁሉም የፋኖ ብርጌዶች ጋር ምሥጢራዊ ግንኙነት አድርጎ በአንድ ሰዓት ውስጥ በሁሉም የክልሉ ክፍለ ሀገራት በ54 ትላልቅና ትናንሽ ከተሞች የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ፈጸመ።
ደብረ ብርሃንን፣ ጎንደርን፣ ባህርዳርን በከፊል፣ ደብረ ማርቆስን እና በርካታ ከተሞችን ለስድስት ቀናት ተቆጣጠረ። በመጀመሪያው የስድስት ቀናት ማጥቃት 54 ከተሞችን ሲቆጣጠር ከፋኖ አንድነት ምክር ቤት 55ሺ ተዋጊዎች ውስጥ የተሳተፈው ግማሹ ቢሆን ነው። በበጌምድር እና በተለያዩ ቦታዎች የነበሩት ብርጌዶች ሊነሱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመመከት በተጠንቀቅ እንዲቆዩ ተደረገ። ይህ 55ሺ ኃይል ይባል እንጂ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚገመተው የአማራ ባለ ጠመንጃ በብዙ ቦታ ተካፋይ ሆኖ ድሉን አፋጥኖታል።
ህወሓት በ17 ዓመታት ሊገነባ ያልቻለውን ኃይል ፋኖ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ እንዴት ማሰባሰብ፣ ማሰልጠን፣ ማቀናጀት ቻለ?
እንዴትስ ባንክ መዝረፍ ቀርቶ አንድ ብር ወድቃ ቢያይ የማያነሳ በጎ ምግባር ያለው ምሥጉን ኃይል ገነባ?
በተቃራኒው አገራችንን ይወክላል የተባለው የአገር መከላከያ ሴት የሚደፍር፥ ገዳም የሚያወድም፥ ወንድ የሚሰልብ፥ ሱቅ የሚዘርፍ፥ አብያተ እምነቶችንና ዩኒቨርሲቲዎችን ምሽግ አድርጎ እንደ ላሊበላ ያሉ ቅርሶች ላይ የሚተኩስ ኃይል ሆነ፡፡ በሕዝብ ላይ ከሰማይ ቦንብ የሚያዘንብ ብልሹ ሥነ ምግባር ከሚያሳይ ሠራዊት አንፃር ፍጹም ተቃራኒ በሆነ የመልካም ምግባር አርዓያ የሆነ ንቅናቄ እንዴት ተፈጠረ? ብሎ መጠየቅ የፋኖን ጠንካራ መርህ፣ አፈጻጸም፣ አቅምና በመልካም ሕዝባዊ ሥነ ምግባር የታነፀ መሆኑን ያስረዳል።
ፋኖ ያለበትን የትጥቅና የተተኳሽ እጥረት ለማቃለል እንዴት በአንድ ሰዓት ማጥቃት ብቻ ከመንግሥት መጋዘኖች በመቶ ሚሊዮን ብር የሚገመት ትጥቅ መቀማት ቻለ?
ፋኖ እንዴትስ 4 ሚሊዮን አባል አለኝ የሚለውን የብአዴንን መዋቅር በስድስት ቀናት ውስጥ ብቻ ማፍረስ ቻለ? ብሎ ለጠየቀ መልሱ ቀላል ነው፡፡
የፋኖ ውጤታማነት ምሥጢሩ ፋኖ ከታች ወደ ላይ በፈቃደኞች የተገነባ በመሆኑ፤ በራሱ ጠመንጃ በየብርጌዱ ተዋቅሮ በነፃነት የሚንቀሳቀስ እና ልሂቃን ከባእዳን በተማሩት በፖሊት ቢሮ በሚሰጠው ትዕዛዝ ወይንም በካድሬ ጥርነፋ የሚታዘዝ የኮሚኒስቶችና የዘረኛ ብሔርተኞች ዓይነት ማሽን ባለመሆኑ ነው። ፋኖ በራሱ የሚያስብ፣ በራሱ ትርፍና ኪሳራውን የሚገምት (risk/reward)፣ በራሱ የሚወስን፥ በተፈጥሯዊው ሰብአዊ ክብር ላይ የቆመ፥ ለሕዝብ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች ራሱን ያስገዛ፥ የሕዝብ እምነቶችንና ባህሎችን የሚያከብር በመሆኑ ተቀባይነቱ ፈጣን ሆኗል።
ፋኖን በሰፊው ግዛትና ስርጭት ውስጥ የሚያስተሳስረውም አንድ ዐላማ፣ አንድ ግብ እና አንድ ማእከል ያለው መሆኑ ነው። ይህ ማእከል ደግሞ “የፋኖ አንድነት ምክር ቤት” ይባላል። የፋኖ አንድነት ምክር ቤት አንጋፋ መባሉም ከሁሉ አስቀድሞ የተደራጁትን በርዕዮትና በመርሕ፥ በዓላማ ግልጽነት አስተባብሮ በመያዙ ነው፤ በመዋቅር ሰንሰለት በዚህ ስብስብ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ያልገቡ፥ በትግሉ ስፋትና ፍጥነት አስገዳጅነት በየቦታው በየጊዜው የሚፈጠሩ የፋኖ አደረጃጀቶችን በማሰባሰቡ፣ ያለውን በማካፈሉና በመረዳዳቱ ነው። ለሀገሩ ለወገኑ ህይወቱን ሊሰጥ የመጣውን ወጣት ቅድመ ሁኔታ እያስቀመጠ ይሄንን ካደረግክ እኔ በስምህ የለመንኩትን ብር እሰጥሃለሁ ስላላለ ነው። ያለውን ያካፍላል፣ በአንድ ላይ ይታገላል፣ በአንድ ጉድጓድ ይቀበራል እንጂ ትልቅና ትንሽ ባለቤትና ጭሰኛ ዓይነት ስሜት አይፈጥርም።
የፋኖ አንድነት ምክር ቤት መቼ፣ እንዴት፣ በማን እንደ ተፈጠረ?
የፋኖን አመራርና መሪነት በሚመለከት በበርካታ ሚዲያዎች የምናየው ግራ መጋባት፣ ፋኖ በኮሚኒስቶቹ አደረጃጀት ተጠርንፎ እንደ ኮ/ል መንግሥቱ ወይንም እንደ አቶ መለስ ዜናዊ ከፍ ብሎ የወጣ እና ሁሉን አውቃለሁ የሚል አንድ አንባገነን ከፊቱ ስላላቆመ ነው። ፋኖ በተቻለ መጠን በጋራ ስምምነትና በጋራ አመራር እና የምክክር ውሳኔ (collective leadership & consensus building) የሚከተል ነው።
ፋኖ የእነ መለስን የእነ አብይን አንባገነንነት እያወገዘ በእነሱ አምሳልና ተግባር “ቆራጡ” “ታላቁ” የሚባል ሥርዓት ለመገንባት አይፈልግም። ፋኖ የአንድን አገር ዜጎች ከፋፍሎ ለአንዱ ልዩ መብት ለሌላው ደግሞ መብት አልባ፣ አንዱን እዳ ከፋይ ሌላውን አስከፋይ አድርጎ ደልድሎ የሚሰጥ ሳይሆን ዜጎች ሁሉ በሰብአዊ ክብራቸው በየትኛውም ማእዘን ሙሉና የማይሸራረፍ እኩል መብትና ነፃነት እንዳላቸው የሚያምን ነው። ሰው ሁሉ እኩል አይደለም፣ አንዱ ልዩ ጥቅም ሌላው ደግሞ ልዩ ጥቃት ይገባዋል ብሎ ፈርጆ በሠራዊት ኃይል ረግጬ እገዛለሁ ያለውን ሥርዓትና ርዕዮት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከጫንቃው ለማስወገድ የተነሳ ኃይል ነው።
ስለዚህ ሚዲያውም ሆነ በዲያስፖራ ያላችሁ ወዳጆች አንድ መሪ እና ለመሪው ታዛዥ የሆነ አንድ ኮሚኒስታዊ የመሰለ ጠንካራ (Vanguard) ድርጅት አትናፍቁ። አብይ አህመድ ሲመጣ የጨፈረው እና ለብርሀኑ ነጋ በአዲስ አበባ ስታዲየም የጮኸው የዋሑ የአገራችን ሕዝብ የልሂቃንን ክህደትና አስመሳይነት ካስተዋለ በኋላ ያደረገውን በቪዲዮ መልሶ ለማየት እንኳ ይሸማቀቃል። ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የሆያ ሆዬና የመንጋ ፓለቲካ ሳይሆን በስሌትና በቀመር የሚመራ፥ የታወቀ እሴትና መርሕ ያለው፥ አገራችንን እያጠፉ ከሚገኙት ዓይነት የቁማርና የማጭበርበር ፖለቲካ ራሱን ያጸዳ ትግል ነው። ስለዚህ ከስህተታችን እንማር፤ በዚህ መንገድ ተናብበን ከተጓዝን ይሄንን ስርዓት በቶሎ እንደምናስወግደው ጥርጥር የለንም።
ሌላው፣ ሁሉም ሊረዳው የሚገባው ፋኖ ነጻ አውጪ አይደለም፤ ማንንም ነጻ ማውጣት አይፈልግም። ቁጭ ብሎ በባርያ ሥነ ልቦና ነጻ አውጪና መፍትሔ ሰጪ ልዩ ወገን የሚጠብቅ፥ ዋጋ ሳይከፍል ከመጣው ጋር ሁሉ በአድርባይነት እየተቃቀፈ ግፍን የሚያስቀጥል ትውልድ እንዲቀጥል፣ ራሱን “ነጻ አውጪ ነኝ” በሚል ትምክህትና በነፃ አውጪነት ስም ራሳቸውን ወደ ለየላቻው አምባገነን፥ ዘራፊና ጨፍጫፊ ቡድን ዓይነት ባህል ማስቀጠል አይፈልግም።
የፋኖ ተግባር ሁሉም ራሱን ነጻ እንዲያወጣ የሚችልበትን መደላድል መፍጠር ነው። ራሳቸውን ነጻ ያወጡ ሰዎች ናቸው ነጻ አገር መፍጠር የሚችሉት ብሎ ፋኖ ያምናል። ኢትዮጵያም ነጻ አገር ሆና በነጻነት የኖረችው ነጻ ዜጎች ስለመሠረቷት ነው። ኢትዮጵያ በዘመናዊ ሠራዊት ሳይሆን አራሽ፣ ተኳሽ፣ ቀዳሽ ነጻ ህዝብ ስለነበራት ነው በነጻነት የኖረችው። ነጻ ህዝብ ሌላውን የሚጠብቅ ሳይሆን በራሱ ትጥቅ፣ በራሱ ስንቅ፣ በራሱ እቅድ ህይወቱን የሚሰጥ ህዝብ ማለት ነው፡፡
ፋኖ በመደብ፣ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት ማንንም ወገን ባሪያና ጌታ አድርጎ አልፈረጀም። ፋኖነት መርሖዎቹ፥ እሴቶቹ፥ ታሪኩና እምነቱ ይህን ዓይነት ከፋፋይነት እንዲፈጽም አይፈቅድለትም።
ፋኖ የሕዝብ ህልውና እና የአገር በአንድነት መቀጠል አምጦ የወለደው ጤናማ ሰብእና ያለው ኃይል ነው። የፋኖ ተጋድሎም በስሑት ርእዮት፥ በሐሰተኛ ትርክት ተነድተው፥ የግል የሥልጣን ጥማቸውን ለማርካት ከባእዳን ጋር በመተባበር ሰብእናቸውን ሸጠው፥ በሕዝብ ግብር እና በሕዝብ ሀብት የገዛ ወገኖቻቸውን ከፋፍለው ከሚያጠፋፉ የማፍያ ልሂቃን ለመላቀቅ እና የጥፋታቸው ማስፈጸሚያ የሆነውን ሥርዓት ለማስወገድ የሚደረግ ተጋድሎ ነው።
ፋኖ እያንዳንዱ ዜጋ ከዘረኛ የጎሣ ልሂቃንና ከፈጠሩት የጭቆና ሥርዓት ቀንበር ሥር ራሱን እንዲያወጣ የሚያደላድል ኃይል እንጂ ነፃ አውጥቼሃለሁና ከአንተ በላይ ልሁን እያለ ልዩ ጥቅም ያላቸውና የሌላቸው፥ መኖር የሚገባቸውና መጥፋት የሚገባቸው፥ መበልጸግ ያለባቸውና መደኽየት የሚገባቸው በማለት የአሁኑ ሥርዓትና ቀዳሚው ያደረገውን የሚያስቀጥል ከሰብአዊነት ውጪ የሆኑ ኅሊና ቢሶች፥ ፈሪሃ እግዚብሔር የተለያቸው ጥቂት ልሂቃን የሤራ ውጤት አይደለም። ነጻ አውጪዎች የሚሰጡና የሚነሱ ስለሆኑ የተደራጀና በራሱ የሚተማመን ዜጋ ደግሞ መብቱን ከመስጠት ሞቱን ይመርጣልና እንደ ፋኖ ራሱን ነጻ ለማውጣት የቆረጠ ሁሉ ለነጻነቱ ዋጋ እንዲከፍል አርዓያ የሚሆን ነው። ይህንን የተረዱ ግለሰቦች፣ ለመብታቸው ህይወታቸውን ለመስጠት ስለተዘጋጁ ነው የፋኖ ማዕበል የተነሳው። ራሱን ነፃ ለማውጣት የተነሳና የተዘጋጀን ሕዝብ ከሩቅና ከዳር ቆሞ መሪና አመራር ልስጥህ ማለት የፋኖን ዓላማ አለመረዳት ነው።
በሌላ በኩል፣ እንዴት ፋኖ በስድስቱ ቀናት ማጥቃት በርካታ እስር ቤቶችን ደርምሶ በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ፓለቲከኞችን ከሚማቅቁበት እሥር ቤቶች ማስፈታት ቻለ ብለን ከጠየቅን የፋኖ ትግል ውጤት ያለ መሪ፣ ያለ ቅንብር፣ ያለ ትብብር እንዳልመጣ መገንዘብ እንችላለን። ይህም የሆነበት ምክንያት በማርክሲስቱ አደረጃጀት አምስት ወይንም ሰባት መሪዎች የፈጠሩት ሳይሆን ከታች ወደ ላይ መሪ እየፈጠረ እያሳደገ በመምጣት ላይ ያለ ድርጅት ስለሆነ ነው። መሪዎቹ ፎቶአቸው ካልተለጠፈ፥ እኛ ካላወቅነው፥ በሚዲያ ቀርቦ ወይንም ቀርባ ካልተናገረ/ች መሪ የለውም ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። በተግባር የተፈተኑ መሪዎች ከመፍጠር ይልቅ ተሽቀዳድሞ ድርጅቱን በገንዘብ ለመግዛት ወይንም በሚዲያ በሚገነባ የሐሰት ምንነት ድርጅቱን ለመቆጣጠር መሞከር ድርጅቱን ያዳክማል እንጂ ውጤታማ አያደርገውም። አሁን በሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ እየተሞከረ ያለው አካሄድ ድርጅቱን ይጎዳልና ይመከሩ የምንለው ለዚህ ነው።
ፋኖ ከተማሪ እስከ ፕሮፌሰር፣ ከአራሽ ገበሬ እስከ ሀኪም፣ ከተራ ጀሌ እስከ የወታደራዊ ጠበብትና ኮሎኔሎች፣ ከዘመናዊ ትምህርት ምሁራን እስከ ጥልቅ የሃይማኖታዊ እውቀት ያላቸው ሰዎች ስብስብ ነው። ከዚህ ውስጥ መሪ አይወጣም ማለት ለህዝብም ለታጋዮቹም ንቀት ያስመስላል። የፋኖ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ በሚዲያ የሚነበብ ሳይሆን አመራሮቹ ሰውን ያከበሩ፥ ለኅሊናቸው የታመኑ፥ ፈሪሐ እግዚአብሔር ያላቸው፥ የአገራቸውን ረዥም ታሪክ በደማቸው ለማስቀጠል የቆረጡ፥ ከአገር-በቀል እስከ ዘመናዊ አስተሳሰቦች መርምረው የተረዱ እንዲሆኑ ይፈልጋል። ከዛላ አንበሳ እስከ ቶጎ ጫሌ፥ ከአክሱም እሰከ ሞያሌ፥ ከቤኒሻንጉል እሰከ ደዋሌ በተዘረጋው ብዝኃነት ያለው የአገራችን እውቀቶች፥ እሴቶችና ልዩ ልዩ ፍላጎቶች ታሳቢነት የተቀመረ ፍልስፍና ያለው ስብስብ ነው።
እንዲታወቅልን የምንፈልገው፣ ፋኖ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሁሉ እንደተለመደው በጥቂት ምሁራን አእምሮ ስፋት ልክ በተሰፋ ጠባብ ማኒፌስቶ ውስጥ ማስገባት የሚያሻው ኮሚኒስታዊ ወይንም የሌላ ውጭ-ገብ ፖለቲካዊ ቀመር ባርያና አምላኪ አይደለም። ፋኖ ልሂቃን ለሚጽፉት ማኒፌስቶ ወይንም ሕገ መንግሥት ተብዬ የሕዝብ ማፈኛ ባርያ ሆኖ የሚገድልና የሚሞት ሰው የተሰበሰበበት የአብዮተኞችና የነፃ አውጪዎች መንጋ አይደለም። ፋኖ ከውልደቱ የተውሶ ፍልስፍና አንጠልጥሎ ጥራዝ ነጠቅ ሆኖ በመደብ ክፍፍል፣ በሃይማኖት፣ በጎሳ፣ በክፍለ ሀገር ወይንም በጎጥ፥ ወይንም በዘረኛ የጎሣ ፍልስፍና ህዝብን የሚያጋጭ አይደለም። የአማራን ገጽታና ባህርይ ይዞ የተወለደ፥ ሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነባር እሴቶች ምርኩዝ ያደረገ አገር በቀል የህልውና ተከላካይ ኃይል ነው። ኢትዮጵያ ያላት በጎ ነገር ሁሉ ፋኖ በውስጡ ይዞት ተገኝቷል። ፋኖ የሚበልጥ ወይንም የሚያንስ ብሔር፥ ልዩ ጥቅም የሚሰጠውና የሚከለከል፥ የሚሰደድና የሚያሳድድ፥ ካሣ የሚያስከፍልና የሚከፍል፥ የታሪክ ባለቤት የሆነና ታሪክ አልባ፥ መልካምና ክፉ፥ ጨቋኝና ተጨቋኝ ብሎ መድቦ የተነሳ አይደለም። ሕዝባቸውን ለ50 ዓመታት ያለማቋረጥ ከፈጁ፥ ካፋጁና አሁን እያጠፋፉ ከሚገኙት ከነፃ አውጭዎችና የነፃ አውጭዎቹ ልጅ ከሆነው ብልጽግና መንግሥት ጋር ፈጽሞ የሚቃረን ነው። ፋኖ በከተማም በገጠርም በመላው ኢትዮጵያ ያለ እና ስሩን እየሰደደ ያለ ድርጅት ነው። የኢትዮጵያን ባንዲራ አስቀድሞ ይዞ የሚታገለው ለሁሉም የተሻለ አገር ለመፍጠር ነው። ፋኖ የሚታገለው ስለራሱ መብትና ነጻነት እንጂ በጠላትነት ፈርጆ የሚደመስሰው መደብ፣ ብሔር፤ ሃይማኖት፥ ባህልና ማኅበረሰብ የለውም።
የፋኖ ተግባርና ዓላማ በሚከተለው መዝሙር ግልጽ ሆኖ ተቀምጧል።
“ኢትዮጵያዊነት ውድ መልኬን ነጋ ጠባ አትነካኩት፤
አላወልቅም ባንዲራዬን ልቤ ላይ ነው የለበስኩት፤
ከልቤ ላይ አላጠፋም የአበሻነት ታሪክ ውርሴን፤
እሰዋለሁ ለአንዲት ሀገር አንድ ነፍሴን፤
ፋኖ ለነጻነት፣
ፋኖ ለአንድነት፣
ይዘምታል ምን ጊዜም ለኢትዮጵያዊነት፡፡
ሜዳ ገደል ፀሀይ ብርዱን አልፈዋለሁ ሁሉን ችዬ፤
ለሕጻናት ለአዛውንቱ ለሰው ክብር ብቻ ብዬ፤
ለነጻነት ብዬ፡፡
የአባቶቼን ፈለግ ስለምደጋግም፤
የበላይን ታሪክ ከታች አላደርግም፡፡
የፋኖነት ገድል የፋኖነት ክብሬ፤
ብሞትም ላንድ ሀገር ብኖርም ላገሬ፡፡
አቤት ብዬ ተጠርቼ ተሰልፌ በፋኖ ስም፤
የተሰዉ ጓደኞቼን የደም ዋጋ አላረክስም፤
የደም ዋጋ አላረክስም፡፡
ፋኖ ለነጻነት፣
ፋኖ ለአንድነት፣
ይዘምታል ምን ጊዜም ለኢትዮጵያዊነት፡፡”
ዓላማውም
አማራውን ከእልቂት የኢትዮጵያን ሕዝብ ደግሞ ከጭፍን የጥጋበኞችና ባለጊዜዎች መዳፍ ሥር በማላቀቅ ሁሉም በአገሩ የሰብአዊ ዜግነት ሙሉ መብቱን እንዲያስመልስ፥ በአገሩ ጉዳይ ሙሉ ባለቤት እንዲሆን አርዓያ ሆኖ ማሳየት ነው።
የአማራ ፋኖ “ሰው ሰው” የሚሸት ተፈጥሮን በትርክትና በጠባብ ልሂቃን ትርጓሜ የማይቀይር የሙሉ ሰብእና መገለጫነቱን በተግባር እየገለጸ የሚገኝ ስለሆነ አማራን በመጥላት የኖሩ ፖለቲከኞች ሳይቀሩ ስለ ፋኖ ክፉ መናገር አልተቻላቸውም። በዘረኝነት፥ በሐሰተኛ ትርክት፥ በተውሶ ባገኙት ውጭ-ገብ ኢሰብአዊ ነፅሮተ ዓለም ተመርተው አገራቸውን ለ50 ዓመታት ያደሙና በመንግሥትነት ደረጃ ነውረኝነትን ሕጋዊ ያደረጉትን ነው ፋኖ የሚታገለው። ሕዝብ በመፍጀት፥ ዜጎችን ከፋፍሎና አንዱን የበላይ ባለ መብትና ባለአገር፥ ሌሎቹን ደግሞ መጤ የሚያደርግ ስርዓትን ለመዋጋት ነው። ሴት የሚደፍር፥ የሃይማኖት ቦታዎችን የሚያወድም፥ ገበሬዎችን እንዳያመርቱ ግብዓት የሚነፍግ፥ በሐሰተኝነትና በሤራ ተወልዶ በሤራ አገር ለመምራት ደፋ ቀና የሚለውን ለማስወገድ ነው።
የፋኖ አንድነት ምክር ቤት ውጭ ግንኙነት ስህተት
በእርግጥ እንደ ፋኖ አንድነት ምክር ቤት፣ በውጪ ሀገር ያሉ ወገኖች ድጋፍ በማሰባሰብና መንግሥታትን የማግባባቱን ስራ በተሻለ ይሰሩታል በማለት ለጽሁፍ ትኩረት አልሰጠንም። የኛው ናቸው የምንላቸው የጎደለውን አሟልተው የተጣመመውን አቃንተው መልዕክታችንን ያደርሱልናል በማለት ችላ ብለነው ነበር። ይሁንና ይረዱናል ብለን የጠበቅናቸው ወገኖቻችን ፋኖ “አንድ አይደለም፣ አይግባባም፣ ዓላማና ግብ የለውም፣ ማኒፌስቶም አልጻፈም” ወደሚል ትርክት ሄዱ። ይህ ደግሞ “እኛ እናደራጀዋለን፤ እኛው እንምራችሁ” ወደሚል እያደገ ሲመጣ የፋኖ አንድነት ምክር ቤት የራሱን ትርክት እራሱ መጻፍ እንዳለበት ተረዳ።
አሁን የፋኖ አንድነት ምክር ቤት የራሱ ድህረ ገጽ፣ የራሱ ዩትዩብ፣ የራሱ ርዕሰ አንቀጽ ትንተና፣ የፋኖ ድምጽ ተብሎ የተሰየመ ዓምድ ይኖረዋል። ለመረጃ ያህል ለወደፊት በአደረጃጀት ላይ የሚገኘው ገጹን ይከታተሉ። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን የፋኖ አንድነት ምክር ቤት ማን ነው? የት ተመሰረተ? ምን ተስፋና አደጋ ይታየዋል? የሚለው በዝርዝር ከክፍል ሁለት ጀምሮ በተከታታይ ይቀርባል። ይከታተሉን።

ክብር ለጀግና ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፡
መጨቆን መታረድ መገደል ሰለቸኝ ብለው ትጥቅ ላነሱ፣ በትግሉ ውስጥም ለተሰዉ፣ አካላቸው ለጎደለ፣ በእስር ለሚማቅቁ አባሎቻችን ያለን ክብር ከፍ ያለ ነው። እነሱ የሞቱለትን፣ የደሙለትን፣ በእስር የተንገላቱለትን ዓላማ ከግብ ሳናደርስ እንደማንቆም በድጋሜ ቃል እንገነባለን። በአማራ ሕዝብ ላይ የተደቀነውን የመጥፋት አደጋ አስወግደን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሰላም ወጥቶ የሚገባባት፣ በህግ ፊት እኩል የሚታይባት፣ በፈለገው ቦታ ተንቀሳቅሶ፣ ሰርቶ፣ ከብሮ የሚኖርባትን ኢትዮጵያ ሳናስመልስ አንቆምም፣ አናንቀላፋም፣ አናርፍም።

አማራ በትግሉ ህልውናውን ያስከብራል!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *