ዚዝምና መንግሥታዊ የፕሮፓጋንዳ ትርክት

(ምንና ምን?)

የናዚ አረመኔ የጦርነት ማሽን የሰውን ነፍስ ለመብላት ማጓራት የጀመረው በመጀመሪያ በሌላ በማንም የውጪ ኃይል ላይ ሳይሆን፣ እንደ ማኅበረሰብ የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ደርሰዋል ብሎ ጠምዶ በያዛቸው በጂዊሽ ኮሙኒቲዎች ላይ ነበር።

የናዚ ፓርቲ ሲመሠረት ከመነሻው ጀምሮ የነበረውን ታሪክ የሚነግረን እጅግ ተነባቢውን መፅሐፍ ያበረከተልን የታሪክ ፀሐፊ ዊልያም ሺረር ነው።

በዚህ መፅሐፉ ሺረር የሚነግረን የመጀመሪያዎቹ አምስት የናዚ አባላት ገና በ1924 ላይ፣ The Elders of Zion የሚባለውንና እውነት ይሁን ውሸት የማይታወቀውን ከምዕራብ ሩሲያ (ምናልባትም ከዩክሬይንና ከፖላንድ) አካባቢ ይኖሩ የነበሩ የጂዊሽ አባቶች፣ ሀገሮችን ከውስጥ ገብተው በማፈራረስ፣ ዓለምን በቁጥጥራቸው ሥር ለማዋል የተማማሉበት ሰነድ የተባለውን ኮፒ ይዘው፣ በጀርመን ባሉ ትውልደ እስራኤላውያን ላይ፣ ተነግሮ የማያልቅ ዘርፈብዙ የጥላቻ መዓት ለማስፋፋት ሱ ሲዶልቱ እንደነበረ በዝርዝር ስምና ቀን እየጠቀሰ አስቀምጦልን እናገኛለን።

የሂትለር የፕሮፓጋንዳ ቀኝ እጅ ሆኖ በሚዩኒክ ፓርቲውን የተቀላቀለው (እና የሚዩኒክ ከንቲባም የነበረው)፣ በሙያው የስነፅሑፍና ትያትር ዶክተር የሆነው ጆሴፍ ጎብልስ፣ ጂዊሾች ላይ የከፈተውን የማጥላላት ዘመቻ በዘመኑ በነበሩት የብዙሃን መገናኛ ዘዴዎች በሬዲዮና በጋዜጣ ብቻ ማካሄዱ አላረካውም። ህዝቡ የጂዊሾችን ማንነት በዓይኖቹም ጭምር ማየት አለበት ብሎ ደመደመ።

ስለሆነም በ1937 መጨረሻ ገደማ (በህዳር)፣ የመጀመሪያውን ጂዊሾችን የሚያጥላላ “ዝንተ ዓለማዊው ወይም ዘላለማዊው ጂዊሽ” የሚል ታላቅ ኤግዚቢሽን በሚዩኒክ ከተማ ከፈተ። በዚያ ላይ ጂዊሾች በሠይጣን፣ በኢሉሚናቲ፣ በመልዓከ ሞት አፅም፣ እና የሕዝቡን ደም መጥጠው ያበጡ ቦርጫሞች፣ ሥራን የማይወዱ፣ ተቀምጠው ከሚለፋው ህዝብ አፍንጫ ደሙን የሚቀዱ ተቀምጦ በዪዎች አድርጎ አቀረባቸው።

ያ ኤግዚቢሽን በሚዩኒክ ብቻ ሳይሆን በመላዋ ጀርመን እየተዘዋወረ በትንሹ 400 ሺህ ተማሪዎችና ወጣቶች እንዲያዩት አድርጓል።

ከዚህም አልፎ ልክ በሶሻሊስታዊው ዘመን ባላባቶች ተብለው የሚሣሉ ቦርጫቸው የተነፋ (ቀፈታም) ሰዎች፣ ምርር ያለውን አጥንቱ የወጣውን የምስኪኑን ሕዝብ ጡጦ ከአፉ ላይ ቀምተው ሲመጠምጡበት፣ ህፃኑ ምርር ብሎ ሲያለቅስ፣ የመሣሰሉት የፕሮፓጋንዳ ፖስተሮች ሁሉ፣ ጂዊሾችን እንደ ባላባቶች፣ ጡጦ የተቀሙትን ደሞ እንደ ጀርመን ድሆች እያደረጉ የሚያቀርቡ ፖስተሮች በመላዋ ጀርመን በየአደባባዩና ግድግዳው እንዲለጠፉም አስደርገዋል ናዚዎች።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *