ከአማራ ፋኖ በጎንደር የተሰጠ መግለጫ

የዐማራ ሕዝብ ከትናንት እስከ ዛሬ የመንግሥትን ሥልጣን በተቆናጠጡ ዐማራ ጠል ኃይሎች አማካይነት ፖሊሲን፣ ሕግንና ሥርዓትን ሽፋን ባደረገ መልኩ በመላው የኢትዮጵያ ግዛት እንደ አውሬ እየታደነ ተገድሏል፣ በጅምላ ተቀብሯል፣ አስከሬኑ ሳይቀር በእሳት
ተቃጥሏል፣ ለአራዊትም ሲሳይ ሆኗል። ይህን ተከትሎ ሕዝባችን ለበርካታ ዓመታት በሰላማዊ ትግል የጠየቀ ቢሆንም ይህ ሠላማዊ ትግላችንና ጥያቄያችን እንደ አቅመቢስነት፥ አላዋቂነትና ሞኝነት ተቆጥሮ መንግሥት ነኝ የሚለው ሥርዓት በመላው ኢትዮጵያ ከሚፈጽመው ዘር የማጽዳት ተግባሩ በተጨማሪ የመኖሪያ ቀያችን ድረስ ወታደር አዝምቶ ጭፍጨፋ በመጀመሩና በግልጽ ተፈጥሯዊ የመኖር ጸጋችንን ሊነጥቀን በመሞከሩ ሕዝባችን ከአጠቃላይ ጥፋት ራሱን ለመከላከል በየቀጠናው መንግሥት መሩን የዘር ማጥፋት ዘመቻና
ጭፍጨፋ ለመፋለም ተገድዷል። ለዚህም ለበርካታ ወራት በማኅበረሰቡ ውስጥ በሚገኘው ባህላዊ አቅሙ ከመፋለም ጀምሮ ወታደራዊ ቅርጽ ያለው አደረጃጀቶችና ሥልጠና በማከል ራሱን የአጥፊዎቹን አቅምና ፍላጎት ለማምከን በሚያስችል ደረጃ የማጠናከርና የማሳደግ
ላይም አተኩሮ በአራቱም የዐማራ ጠቅላይ ግዛቶች ታላላቅ መሠረታዊ ተግባራትን አከናውኗል።
ይህ ትግል ወቅቱን እየዋጀ፣ የሕዝባችንን ህልውና በሚያረጋግጥና ጠላትን ሙሉ በሙሉ ማሸነፍ በሚያስችል መልኩ ወደ ተሟላ አደረጃጀት እያደገ መምጣቱ የተረጋገጠ ሐቅ ነው።
ግብረ ባንዳዎች ያልተፈጠረ አደረጃጀት እንደሆነ በአርበኞችና በሕዝባችን የታመነ ጉዳይ ነው።
መሠረታዊ ሐቁ ይህ ሆኖ እያለ በቅርቡ የተመሠረተው የጎንደር እዝ ብዙ ያልተመከረበት፣ አስመራጭ ኮሚቴዎች መሬት ላይ ካሉት አደረጃጀቶችና ታጋዮች ይልቅ ከጀርባ ካሉ ስውር ፍላጎትና አጀንዳ ካለቸው አካላት ጋር ብቻ የመከሩበት፣ የእዝ መሪዎች ሳይቀር በጨዋ ደንብ ሳይተቹ ወደ መሪነት የመጡበት፣ የትኛውም የክፍለጦር አመራር ያልተሳተፈበት ከውጭ ሆነው የራሳቸውን ፍትወት ለማስፈጸም በሚታትሩ አካላት ይሁንታ ላይ የተመሠረተ የእዝ አደረጃጀ መሆኑን መግለጽ እንወዳለን። በዚህም በርካታ አርበኞች ቅሬታቸውን በተለያዩ ጊዜያት ቢያቀርቡም ጉዳዩን በሰከነ መልክ ተመልክቶ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ
የይስተካከል ጥያቄና ቅሬታ ያቀረቡ አርበኞችን በየሚዲያው እየወጡ ጭቃ መቀባት በከፍተኛ ደረጃ አሳዝኖናል፣ ለአባቶቻችንም ያለን ክብር ከፍ ያለ ቢሆንም በቅንነትና የዋሕነት በሩቅ እጆች ተታለው ወይም ባላወቁት ተንኮል ተጠልፈው መገኘት የማይገባቸው ቦታ ላይ በመገኘታቸው ከፍተኛ ቅሬታ ፈጥሮብናል። ቅሬታችን በመታለልም ይሁን በመደለል ይህን ለትግሉ እንቅፋት የሚሆን ሂደት ውስጥ የገቡ የተከበሩ አርበኛ አባቶቻችንና ወንድሞቻችን የትግሉን የሩቅ ጉዞና የአማራ ሕዝብና አገራዊ ህልወናን ያላገናዘበ ስሜታዊና
ጠባብ ምልከታዎች ያደነቃቀፉትን ይህን መንገድ እንዲተዉ እየመከርን ሂደቱ የአማራ ሕዝብን ታላቅነትና የሚጠብቀውን ውጤት የማይመጥን መታረም ያለበት እንደሆነ ለመግለጽ ተገደናል። በዚህ ጎታች የትግል አካሄድም ቢሆን ሕይወት እየገበርን የምንገኝ አርበኛ ጓዶች ጠላት
የዘራው ክፉ የመለያየት አረም እስካልተነቀለ፣ መሬት ላይ ያለን ጓዶች መሃላችን የገባውን የሚለያይ ሃሳዊ ጠላት አሽቀንጥረን እስካልጣልንና ጋርዮሻዊ የትግል መስመር ለመዘርጋት ምቹ ሁኔታዎች እስካልተፈጠሩ ድረስ እንዲሁም እውነትን፣ ፍትሕን፣ ቅንነትን፣ ሕዝብ ማስቀደምን ማእከል ያደረገ የትግል መስመር መቀየስ ያደረግነው ከሚዲያ የተሰወረ አሰልቺ ሙከራና ምልጃ ማብቃቱ ግድ በመሆኑ ከዛሬ ጀምሮ የራሳችንን እዝ የመሠረትን መሆናችንን ለሕዝባችን ማሳወቅ እንፈልጋለን።
ይህ የመሠረትነው ዕዝ በማይስተካከል የድንጋይ አለት ላይ የተጻፈ ዶግማ ሳይሆን በውጭና በጠላት እጅ እየተዘወሩም ሆነ እየተታለሉ፥ ወይም ኃላፊ ዝናና ጥቅም እያታለላቸው የአገር ባለቤትነት፥ የፍትሕ፥ የሰብአዊነትን የሰው ልጆች በሉዓላዊት አገር ውስጥ እኩል የመሆን
ታላቁን የህልውና ትግል ዓላማ ሳይጻረሩ ራሳቸውን አርመው ወደ ዕዙ ለመጠቃለል ለሚሹ በመሆኑም በመላው የዐማራ ጠቅላይ ግዛቶች የምንገኝ የፋኖ ጓዶች በየቀጠናችን ያሉ ሥራዎቻችንን እያጠናቀቅን መላው የዐማራ ሕዝብና መላው ኢትዮጵያውያን ተስፋ የሚያደርጉትን ሥርዓት የማዋለድ እንዲሁም በሕዝባችን ጫንቃ ላይ የተጫነውን አስከፊ ሥርዓት አሽቀንጥሮ የመጣል ተግባራችን ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ምንም እንኳን መሬት ላይ የሚታገሉ ልዩ ልዩ የፋኖ አደረጃጀቶች ሕይወት የሚገብሩበትና አንድ የትግል ዓላማን አንግበው የሚሠሩ ቢሆንም ከጀርባቸው የሚገኙ ስውር እጆችና ድብቅ ዓላማ ያላቸው ግለሰቦች፣ ቡድኖችና አደረጃጀቶች የኅልውና ትግላችንን በመጎተትና
በወንድማማቾች መካከል የፈጠሩብን መቃቃር የትግላችን አሉታዊ ታሪክ አንዱ አካል ነው። የዐማራ ፋኖ መነሻና የትግል ሂደት ግፍ፣ ኢ-ፍትሐዊነት፣ ጭቆናና በኅልውና ጥያቄዎች መግፍኤነት የተወለደ በአንጻሩ ዛሬ ላይ ከውጪ እስከ ሀገር ቤት እንደ አሸን በተፈለፈሉ ሁሉ ክፍት የሆነ መሆኑን ከወዲሁ እናሳውቃለን። ለህልውናው ዓላማ የሚታገል፥ የሦስተኛ ወገን መሣሪያ ያልሆነ፥ በጊዜያዊ ጠባብ ጥቅሞች ልጓም ከሩቅ የማይጎተት ማንኛውም ታጋይ በዕዛችን ውስጥ ከአመራር እስከ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አደረጃጀት የመሳተፍ እድሉ ከሁላችንም እኩል ክፍት ሆኖ ይጠብቀዋል። በዚህ መሠረት በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ የሚገኙ በይበልጥ በአማራ ፋኖ አንድነት በጎንደር አደረጃጀት ውስጥ የምንገኝ አርበኛ ጓዶች “የአማራ ፋኖ በጎንደር” በሚል አደረጃጀት የሚከተሉትን የሥራ አስፈጻሚ ኃላፊነት ቦታዎችን በግልጽ መሥፈርት ነውር፣ ነቀፋ የሌለባቸውን፣ ከሦስተኛ ወገን ጋር የተጠላለፈ ከመጎተቻ ገመድ ነፃ የሆኑ፥ ለትግሉ ታላቅ ዓላማ ሲሉ ጊዜ የሚሰጡ ፈተናዎችን የሚታገሱ፥ ለዝናና ለስም የትግሉን ምሥጢር
አውጥተው የማይዘሩ ታግለው የሚያታግሉ አርበኞችን በሙሉ ድምጽ የሰየምን መሆናችንን እንገልጻለን።

  1. ሰብሳቢ——————- አርበኛ ባዬ ቀናው
  2. ም/ሰብሳቢና ወታደራዊ አዛዥ ——— አርበኛ ውባንተ አባተ
    2.1 ም/ወታደራዊ አዛዥ ——— አርበኛ ሳሙኤል ባለእድል
    2.2 የዘመቻ መምሪያ አዛዥ ——— አርበኛ ከፍያለው ደሴ
    2.3 ም/ዘመቻ መምሪያ አዛዥ ——— አርበኛ ግዛቸው አሌ
    2.4 የሥልጠና መምሪያ አዛዥ ——— አርበኛ አምሳሉ ማዘንጊያ
    2.5 ም/ሥልጠና መምሪያ አዛዥ ——— አርበኛ ገ/ሕይወት ማሞ እና
    —— አርበኛ ማንዴላ እያዩ
    2.6 የሎጀስቲክስ መምሪያ አዛዥ ——— አርበኛ ነጻነት ይበልጣል
    2.7 ም/ሎጀስቲክስ መምሪያ አዛዥ ——— አርበኛ አንተነህ ብርሃኔ
    2.8 ወታደራዊ አስተዳደር መምሪያ አዛዥ———አርበኛ ሰሎሞን አጠና
    2.9 ም/ወታደራዊ አስተዳደር መምሪያ አዛዥ— አርበኛ ጸዳሉ ደሴ እና
    —- ሃ/አለቃ ክፍለ ጊዮርጊስ እሸቴ
  3. ም/ሰብሳቢና ፖለቲካዊ ዘርፍ ኃላፊ ——— አርበኛ አራጋው እንዳለ
    3.1 ም/ፖለቲካዊ ዘርፍ ኃላፊ ——— አርበኛ አበበ ብርሐኑ
  4. የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ዘርፍ ኃላፊ —– አርበኛ ኢንጅነር በዬነ አለማው
    4.1 ም/የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ዘርፍ ኃላፊ– አርበኛ ዶ/ር ገደፋው አስታጥቄ
  5. የቀጠናዊ ትስስር ዘርፍ ኃላፊ ———- አርበኛ አማረ አሸንፍ
    5.1 ም/ቀጠናዊ ትስስር ዘርፍ ኃላፊ ———- አርበኛ ባበይ ጌታሁን እና
    —— አርበኛ ብዟየሁ አታላይ
  6. የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ———– አርበኛ አሸናፊ የወንድወሰን
    6.1 ም/ሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ———- አርበኛ ኢያሱ አባተ
  7. ወታደራዊ እቅድና እስትራቴጂክ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ —- ኮሎኔል ታደሰ እሸቴ
    7.1 ም/ወታደራዊ እቅድና እስትራቴጂክ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ–ኮሎኔል አሸናፊ ይሁኔ
  8. የሂሳብና ንብረት አሥተዳደር ዘርፍ ኃላፊ ———- አርበኛ ታምራት ምስጋናው
    8.1 ም/የሂሳብና ንብረት አሥተዳደር ዘርፍ ኃላፊ ———– አርበኛ ጋሻው ሲሳይ እና
    ———- ጌትነት አለባቸው
  9. የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ———– አርበኛ ቴወድሮስ አባይ
    9.1 ም/የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ———– አርበኛ ደመላሽ ካሳ
  10. የመረጃና ደህንነት ዘርፍ ኃላፊ ———– አርበኛ
    10.1 ም/የመረጃና ደህንነት ዘርፍ ኃላፊ ———– አርበኛ
    *
    11.የጽ/ቤት ኃላፊ ———– አርበኛ ረ/ፕ ተስፋሁን አትንኩት
    11.1 ም/ጽ/ቤት ኃላፊ ———– አርበኛ አስምሮ ፍቃዴ መሆናቸውን እንገልጻለን።
    ይህ በእንዲህ እንዳለ የሚከተሉትን መልእክቶች ለትግል አጋሮቻችንና ባለቤቶች ማስተላለፍ እንፈልጋለን።
    ፩ኛ በጎንደር ጠቅላይ ግዛት የምትገኙ እድሜያችሁ ለትግል የደረሰ ወጣቶች በፍጥነት የአማራ ፋኖ በጎንደርን እንድትቀላቀሉና በየቀጠናችን ያለውን የአማራ ሕዝብን የህልውና ትግል አሁን ከሚገኝበት ደረጃ ከፍ እንድናደርገው ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
    ፪ኛ ለመላው ሕዝባችን ማስገንዘብ የምንፈልገው አንድነትንና ወንድማማችነትን ገፊዎች ሆነን ሳይሆን ስሁት፣ ኢ-ፍትሃዊና ሕዝባዊ ወገንተኝነትን ያላማከለ እንዲሁም የውጭ በተለይም “የአማራ ሕዝባዊ ግንባር” እና መሰል ትግል ጠላፊ ስሁት አደረጃጀቶች ፍትወት
    ማስፈጸሚያ ላለመሆንና የሕዝባችንን፣ የተሰው አርበኛ ወንድሞቻችንን አደራ በጠራራ ጸሐይ አሳልፈን ላለመስጠት መሆኑን እንገልጻለን። በመሆኑም ከዚህ የተሳሳተ አካሄድ በቁርጥ ሃሳብ ተመልሰው ለእውነት፣ ለፍትሕና ለሕዝባችን ህልውና አብሮ ለመታገል ስንጥር ያህል እድል
    ከተፈጠረ በራችን ክፍት መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን።
    ፫ኛ ትግላችንን ትግላችሁ አድርጋችሁ፣ የሚዲያን መርህ አክብራችሁ የምትሠሩ ሐቀኛ የሚዲያ አካላት የአማራ ሕዝብን የህልውና ትግል በቅርብ እንዳይቋጭ፣ ከምንም በላይ ከተሳካላቸው ትግሉን በመጥለፍ የሥልጣን መቆናጠጫ ለማድረግ ካልተሳካላቸው ተቆርቋሪና ታጋይ በመምሰል ራሳቸውን በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ በመወሸቅ የዋሐን ወገኖችንን በመሸንገል በፋኖ ስም ገንዘብ በመለቃቀም የሚንቀሳቀሱ፤ ህይወት የሚከፈልበትን ትግል እንደዋዛ በገንዘብ ታጋይ ለመግዛት የሚንጎራደዱ አስመሳይ ጠላቶቻችንን በምርመራ የጋዜጠኝነት አካሄድ ለሕዝባችን እንድትገልጹ ጥብቅ አደራችንን እናቀርብላችኋለን። ይሁን
    እንጅ በገሃድ ከታወቀው ገዥው ሥርዓት በማይተናነስ ደረጃ የትግላችንን ሻጭና ሸቃጭ ባንዳና ሰውር ጠላቶቻችንን በጋዜጠኝነት በሙያችሁ በማጥራት ለሕዝብ እውነቱን ካልገለጻችሁ እናንተም ከጠላት ድርጎ የሚሰፈርላችሁ የጠላት ተባባሪ ጠላቶች በመሆን በገዛ
    ግበራችሁ ስለምትገለጹ ሕዝባችን ራሱን ከእናንተ እንዲጠብቅ በምናገኘው አጋጣሚ ሁሉ በማስተማርና በማንቃት ከጠላት እኩል ዒላማ እንደምትደረጉ መግለጽ እንወዳለን።
    ፬ኛ በውጭ የምትገኙ ወገኖቻችን ፋኖ ከተማሪ እስከ ፕሮፌሰር፣ ከአራሽ ገበሬ እስከ ሀኪም፣ ከተራ ጀሌ እስከ ወታደራዊ ጠበብትና ኮሎኔሎች፣ እንዲሁም የዘመናዊ ትምህርት ጥልቅ እውቀት ያላቸው ልሂቃን ስብስብ መሆኑ ይታወቃል። ነገር ግን ፋኖን መሪ አልባ አድርገው የሚያስቡ ድንበር ዘለል አላዋቂዎች እየፈበረኩ የሚያቀርቡላችሁን አደረጃጀቶች በተለይ
    “በአማራ ሕዝባዊ ግንባር፣ ሕዝባዊ ሠራዊት እና መሰል ስሁት አደረጃጀቶች” በኩል የሚደረጉ ድጋፎችና ሎጀስቲክሶችን ምንም እንኳን ሀብት የሚለግሰው ወገናችን በቅንነት ቢያደርግም፥ አስተባባሪዎች ግን ድብቅ ግብ በማስቀመጥ እና ሀብቱን ትግሉን ለመከፋፈል ወይም ለድብቅ ዓላማቸው ከርክሞ ለማዘጋጀት እየተጠቀሙበት መሆኑን ተገንዝባችሁ ለጠላት እጅ ከመሆን ራሳችሁን እንድትጠብቁ እያሳስብን ለጋስነታችሁና ለትግሉ ዓላማ ያላችሁ ደጋፊነት ሳይሸራረፍ አቃፊ የትግል አደረጃጀቶች በሰከነ ውይይት እንዲመሠርቱ ብቻ በማለም፥ አጥፊዎችና አስመሳዮችንም መሬት ላይ በሚገኙት አርበኞች በኩል ብቻ ተለይተው
    እንዲመከሩና እንዲስተካከሉ ከማድረግ ያለፈ በስልክ ጭቅጨቃ፥ በዶላር ማባበያና፥ በብልጣብልጥነት የሚደረግ ጣልቃ ገብነትን በንቃት በመከታተል እንድትከላከሉ በአክብሮት እንጠይቃለን።
    ፭ኛ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለጠላት ተንኮል ማስፈጸሚያ እጀታ በመሆን ለትግላችን ሳንካ እየፈጠራችሁ ያላችሁ፥ በምታድረጉት የጀግነነትና ታላቅ የልምድ ባለቤትነት የምናከብራችሁ አባት፥ ወንድምና እኅት አርበኞች፣ ምሁራን፣ ግለሰቦችና አደረጃጀቶች በሕዝባችን የህልውና ትግል ውስጥ ከምትከፍሉት ከፍተኛ የመስዋዕተነት ዋጋ ጋር ፈጽሞ የሚቃረን በወገንተኝነትና በኢሚዛናዊነት ተግባር እያስቀመጣችሁ ያላችሁት ጥቁር ጠባሳ በታሪክ መዝገብ ላይ የሚሰፍር በመሆኑ እስከ ዛሬ ለሕዝባችን የከፈላችሁት በምንም የማይተመን አኩሪ አስተዋጿችሁ አሁን እያደረጋችሁት ባለው ተግባር ተገልብጦ የምትሸማቀቁበት ስለሚሆን ቆም ብላችሁ አስባችሁ ሐቁን እንድትመረምሩ እንመክራለን። ይሁን እንጅ ይህንን ሁሉ ገሃዳዊና ስውር የህልውና ትግላችን አራሙቻ እያወቃችሁ በሃሳብም ሆነ በግብር የምትደግፉ አካላት እጃችን ላይ ባሉ ማስረጃዎችና በቀጣይም በደኅንነት
    መዋቅራችን አማካይነት በምናጠናቅራቸው ማስረጃዎች ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ የምንገደድ መሆኑን እንገልጻለን።
    ፮) ባደርገነው የዕዝ ምሥረታና ከላይ ባስቀመጥናቸው እጅግ የሚቆረቁሩ መልእክቶች ዱብ ዕዳነት ምክንያት እውነቱን እስክትረዱት ለምታዝኑ የመላው የአማራ ሕዝብ፥ የህልውና አደጋ የተጋረጠባችሁና የአማራ ነፃነትን እንደ ተስፋችሁ ለምትጠብቁ ሌሎች የአገራችን ማኅበረሰቦች፥ ከሁሉም በላይ ራሳችሁን ለሰብአዊነት፥ ለእውነት፥ ለፍትሕ፥ ለሀገር
    ባለቤትነት ውድ ነፍሳችሁን የምትከፍሉ የመላው አማራ ፋኖዎች ታላቅ መጽናናት ብቻ ሳይሆን ደስታን የሚያጎናጽፈን እውነትና ትግሉ ከሦስተኛ ወገን ነፃ በሆኑ የሕዝብ ልጆች ብቻ እንዲመራ የተደረገ ውሳኔ መሆኑን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባር የሚመሰክርላችሁ ይሆናል።
    በአጠቃላይ ለአማራ ሕዝብ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስፈልገው የሆያ ሆዬና የመንጋ ፓለቲካ ሳይሆን በስሌትና በቀመር የሚመራ፥ የታወቀ እሴትና መርሕ ያለው፥ አገራችንን እያጠፉ ከሚገኙት ዓይነት የቁማርና የማጭበርበር ፖለቲካ ራሱን ያጸዳ አንድ
    የትግል ተቋም ማዋለድ እንደሚገባ እናምናለን። በመሆኑም ከትናንት ስህተታችን በመማር ሕዝባችን የገጠመውን የህልውና አደጋ ለሰከንድም ሳንዘነጋ ሥርዓቱን አሽቀንጥረን የምንጥልበትን የትግል መስመር የምናደረጅበት ጉዳይ ላይ ብቻ እንድናደርግ በጽኑ እናሳስባለን።
    “ህልውናችን በተባበረ ክንዳችን”
    የአማራ ሕዝብ የህልውና ተጋድሎ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ዋስትናው ይሆናል
    የአማራ ፋኖ በጎንደር
    መጋቢት ፫/፳፻፲፮ ዓ.ም
    ጎንደር፣ አማራ፣ ኢትዮጵያ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *