ከአማራ ፋኖ በጎንደር የተላለፈ የጀግና መሪያችን ሽኝት እና የ‹‹ዘመቻ ውባንተ›› ጥሪ!
አገር ሰሪው ታላቁና ጀግናው የአማራ ሕዝብ ባለንበት በ21ኛው ክ/ዘመን እንደ ሕዝብ ለከፋ የሰብዓዊ ቀውስና ምስቅልቅል ተዳርጎ፣ በሀገሩ ላይ የዘር ማፅዳትና ማጥፋት ዓለማቀፍ ወንጀል እየተፈፀመበት፣ በአገዛዙ የጀምላ ፍጅትና ጦርነት ታውጆበት፣ ህልውናው ከምን ግዜውም በላይ የከፋ አደጋ ላይ ወድቆ ይገኛል።
ይሁንና በዚህ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ የአምደ ፅዮንን ጦር የመዘዙ እልፍ የአማራ ሙሴዎች ጠላቶቹን አምበርክከው የቀደመ ልዕልናውን ለማስመለስ በአንድነት በመነሳት አማራነትን በሞታቸው እያፀኑት ይገኛል። ከእነዚህ ቁጥር ስፍር ከሌላቸው ጀግኖች መካከል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ172 በላይ አውደ ውጊያዎችን በታላቅ ጀብዱ የመራው አርበኛ ሻለቃ ውባንተ አባተ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ከእነዚህ አውደ ውጊያዎች ውስጥ 128ቱን በቀጥታ ግንባር ሆኖ በከፍተኛ ጀብዱ ያዋጋ ሲሆን፤ ቀሪውን 44 አውደ ውጊያዎች ከዋና ማዘዣ ኮማንድ ቦታ በመሆን በጀግንነት፣ በጦር ጥበብና ስትራቴጂዊ በሆነ ወታደራዊ ስምሪት በመስጠት የጠላትን አከርካሪ እንደሰበረ የሻለቃ ውባንተ አባተ የጦር ሜዳ ውሎ ሪከርድ ያስረግጣል፡፡ በዚህም በማይገመት ሁኔታ እጅግ አደገኛ ጸረ-አማራ የአገዛዝ መዋቅር ተተክሎበት የነበረውን ደቡባዊ የጎንደር ቀጠናን ከጠላት በማጽዳት የቴዎድሮስን መንፈስ በክብር ወደቦታው የመለሰ፣ ወትሮም ቀጠናው ይታወቅበት የነበረውን የጀግንነት ካባ በዚህ በኛ ዘመን መልሶ አጎናጽፎታል፡፡ ይህ የማይሞት ታሪክ ሲከወን ሕዝባዊ መሠረቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የጦሩ ገበሬ ሻለቃ ውባንተ አባተ የአዲሱ ታሪክ ምዕራፍ መሐንዲስ ሆኖ ለዘላለም ሲዘከር ይኖራል፡፡
በዚህ የአማራን ሕዝብ ህልውና ለማስቀጠልና የህይወትን መስዋዕትነት ጭምር በሚጠይቅ ተጋድሎ በሚደረግበት ወሳኝ የትግል ምዕራፍ ወቅት፤ መጋቢት 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ የጦሩ ጠበብትና አብሪ ኮከባችን ሻለቃ ውባንተ አባተ ጀግናውን የጉና ክፍለጦር እየመራ የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ አገልጋይ ከሆነው 78ኛ እና 92ኛ ክፍለ ጦሮች ጋር ግማሽ ቀን የፈጀ ትንቅንቅ በማድረግና በመቶዎች የሚቆጠሩ የአገዛዙ ሰራዊትን ከደመሰሰና ከባድ ኪሳራ ካደረሰ በኋላ ደራ ወረዳ ‹ገላዊዴዎስ› አካባቢ በክብር ተሰውቷል።
በጀግናው ሻለቃ ውባንተ አባተ መሰዋዕትነት መላው የአማራ ፋኖ ከፍተኛ የጦር መሪዎች፣ አባላትና፣ የትግል ጓዶቹን ከፍተኛ ቁጭትና እልህ ፈጥሮብናል፤ የማይሞት ታሪክ ሰሪው ሻለቃ ውባንተ አባተ የወጣትነት ዕድሜ ዘመኑን ሙሉ ለአገሩና ለሕዝቡ የሰጠ የቴዎድሮስ ፍሬ፣ የዘመናችን ገብርዬ የጦር ገበሬ ነበር፡፡ ዐርበኛው፣ የአማራ ፋኖ በጎንደር ም/ል እና ዋና ወታደራዊ አዛዥ፣ እንዲሁም የጉና ክ/ጦር ዋና አዛዥ በመሆን በየአውደ ወጊያዎች ላይ ቆራጥ መሪና ጀግና ተዋጊ፣ ሰራዊቱን በወታደራዊ ስነ-ምግባር በማነፅና በማዘመን ልዩ ተሰጥኦ የተላበሰ፣ ቀጠናውን በአጭር ጊዜ ከሽምቅ ውጊያ ወደመደበኛ የግንባር ውጊያ ከማሳደጉም በላይ የትግሉ ባለቤት ሕዝብ እንዲሆን በማድረግ ረገድ በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የብረት ትግሉን እንዲቀላቀሉ ሞራላዊና ቁሳዊ ትጥቅ በተገቢው ሁኔታ እንዲያሟሉ በማድረግ ትግሉን ወደማይቀለበስበት ደረጃ አድርሶታል፡፡
ዐርበኛው የጦር መሪ ብቻ ሳይሆን በንቃተ ህሊና ደረጃ የላቀና ባለምጡቅ አዕምሮ ባለቤት፣ የአማራ ሕዝብ የተጋረጠበትን የሕልውና አደጋ ቀድሞ የተረዳ፣ ውስብስቡን የኢትዮጵያ ፖለቲካ የተገነዘበ፣ የጂኦ-ፖለቲካውን ጠባይ በአደጋው መጠን የተረዳ በመሆኑ የአማራነት አዕማዶች ጎጃም፣ ሸዋ፣ ወሎና ጎንደር አንድነታቸውን በከበረ መስዋዕትነታቸው እንዲያደምቁ የአንድነት ኪዳናቸውን በትግላቸው እንዲያጸኑ ሞዴል ሆኖ የወጣ የዘመናችን ክስተት መሪ ነበር። በተለይም የጎንደር እና የጎጃም ፋኖ በጭስ አባይና በባህርዳር ዙሪያ በጋራ ያደረጓቸውን ወታደራዊ ስኬታማ ኦፕሬሽኖች በማቀናጀት እና በመምራት ጀግናው ውባንተና እርሱ የሚመራው የጉና ክፍለጦር ትልቅ ሚና ነበራቸው።
ፋኖ ሻለቃ ውባንተ ለአማራ ሕዝብ ፍትሃዊ የህልውና ትግል እንደ ሻማ ቀልጦ እራሱን መስዋዕት አድርጎ ትግሉን ወደ ላቀ ደረጃ ያሻገረ አይተኬ የአማራ ልጅ ነው!
ዐርበኛው ቀደሞውኑ ሕዝብንና ሀገርን በታማኝነትና በጀግንነት ለማገልገል የቆረጠ የሕዝብ ጠበቃና የፍትሕ ዘብ የሆነ ጀግና ወታደር ነበር። በቀደመ የሕይወት ምዕራፉ የፌደራል ፖሊስ አባል በነበረበት ወቅት በአማራ ተወላጆች የሰራዊቱ አባላት ላይ ግፍ ሲፈፀም በአይኑ በማየቱ በግፍ ፈፃሚዎቹ ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ጫካ ለመግባት ተገድዶ ነበር። በዚህ ሰበብ በሌለበት የ25 አመት እስር ፍርድ በግፈኛው የትሕነግ/ኢሕአዴግ የጦር ፍርድ ተጥሎበት ነበር። ነገር ግን 2008 የአማራ ሕዝብ አመፅ ሲቀጣጠል ሕዝባዊ ትግሉን በማስተባበር ትልቅ ድርሻ በመወጣት ራሱንና የአማራን ሕዝብ ከጥንተ-ጠላቱ አገዛዝ ነፃ ያወጣ ነባር ዐርበኛ ነበር።
ትህነግ በአማራ ሕዝብ ላይ ዳግም ወረራ ሲፈፀም በዝምታ አላይም በማለትና ሀገር የማዳን ዘመቻውን በመቀላቀል ግንባር ቀደም አብሪ ከዋክብት ከነበሩት መካከል አንዱ ሻለቃ ውባንተ ነበር። ሻለቃ ውባንተ ከወራሪ ኃይሉ ጋር በጠገዴ፣ በማይጠምሪ፣ ደብረ ዘቢጥ፣ በጋይንት፣ በደብረታቦር፣ በፍላቂት፣ በጋሸና፣ በቆቦ እና በተለያዩ አውደ ግንባሮች በተደረጉ ጦርነቶች በመሳተፍ ከፍተኛ ጀብዶች የፈፀመና እና አንፀባራቂ ድሎች ያስመዘገበ ሲሆን፤ በወቅቱ በተደረጉ ተጋድሎዎች አዝማች እና ጀግና ተዋጊ የነፃነት ቀንዲል ነበር። በተለይም በትህነግ ወረራ ወቅት የጋሸናን ምሽግ ሰብሮ የድሉ ብስራት ሳይበር በሌላ አውደ ግንባር የጠለምት ምሽግ የሚደግም የተከዜ ዘብ የእውነተኛው አለም የጀግና ተምሳሌት ነበር። በነዚህ ጦርነቶች ታዲያ ከ 5 ግዜ በላይ ቢቆስልም ከእነ ጉዳቱ እስከ ህይወቱ ህቅታ ድረስ በፅናትና በቁርጠኝነት ታግሏል።
ሻለቃ ውባንተ በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው፣ አስተዳደርና ፍትሕ አዋቂ፣ አንደበተ ርቱዕና የአማራን ሕዝብ የህልውና ትግል መነሻና መዳረሻ ጠንቅቆ የተረዳ ብልህ መሪ ነበር። ጀግናው መሪያችን በማህበራዊ ሕይወቱ ስኬታማ የነበረ፣ በተራዛመ ትግል ውስጥ ሆኖም ቤተሰብ የመሠረተ ባለትዳና የልጆች አባት፣ ራሱን ማስተዳደር የሚችል ሰፊ የእርሻ ስራ፣ የንግድ መኪኖችና፣ የንግድና የመኖሪያ ቤቶች የነበሩት ሁሉ የሞላለት ዐርበኛም ባለፀጋም ነበር። ይሁንና ፀረ-አማራ የሆነው የፋሽስቱ የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ በአማራ ሕዝብ ላይ የጀመረውን የዘር ፍጅትና ሰቆቃ ለማስቆምና ብሎም የአማራን ሕዝብ ነፃ ለማውጣት ሀብት ንብረቱን ጥሎ በርሃ የገባ በተለይም ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ ፋኖነትን ከዐርበኝነት ውርስ ባሻገር ለአማራ ሕዝብ መድሕን ተቋማዊ ሆኖ እንዲጸና ሌት ከቀን የደከመ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በነበረው ሕዝባዊ ትግል የበኩር ልጁን እና ወንድሙን በህልውና ትግሉ አጥቷል፡፡ ዛሬም የራሱን የማይተካ ሕይወት አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ዐርበኛው የዐማራ ፋኖ ሕዝባዊ ትግል ማርሽ ቀያሪ የሆነውን የጉና ክፍለጦርን አደራጅቶ የመራ፣ በዚህም የማይሞት ታሪክ የሰራ፣ በገንዘብና በጥቅማጥቅም የማይደለል የአማራ ሕዝብ የቁርጥ ቀን ልጅ ነበር። የአማራ ሕዝብ ጠላት የሆነው አገዛዙ በሻለቃ ውባንተ ንብረት ጭምር ርካሽ በሆነ መልኩ ውድመት ቢያደርስና ንብረቱን ቢያቃጥልም ለመሪያችን ከአማራ ሕዝብ ህልውና እና ክብር አልበለጠበትም ነበር።
ሻለቃ ውባንተ አባተ ፀረ-አማራና ፀረ-ኢትዮጵያ የሆነውን የብልፅግናን አገዛዝ ለመገርሰስ ዳግም በፋኖነት ወደ ትግል ሜዳ ከወረደበት እለት አንስቶ ያደረጋቸው ውጊያዎችና የፈፀማቸው አያሌ ጀብዱዎች ለታሪክና ለትውልድ ይተላለፍ ዘንድ በደንብ ተዘርዝሮ በባለሞያ መሰነድና ለትውልድ መተላለፍ እንዳለበት በፅኑ እናምናለን።
ጀግናው ሻለቃ ውባንተ አባተ የጎንደር ፋኖ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ወደ አንድ ወጥ አደራጀጀት እንዲመጣና ወጥ አመራር እንዲኖረው ከፍተኛ ጉጉት የነበረውና ለዚህም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በብዙ ሲደክም ነበረ። ከዛም አልፎ ሁሉን አቀፍ የአማራ ፋኖ አደረጃጀት እንዲፈጠር ከጎጃም፣ ከወሎና፣ ከሸዋ የፋኖ አመራሮች ጋር የቅርብ ምክክር እና ስኬታማ የትግል መስክ ትብብሮች ሲፈፅም ቆይቷል።
ለጀብዱ ተፍጥሮ በጀብዱ የተንበሸበሸው መሪያችን ሻለቃ ውባንተ በወጣትነት እድሜው ለዚሁ ሁሉ ስኬት የደረሰው የውስጥና የውጭ ባንዳዎችን፣ የጠላትን መድፍና ታንክን ተቋቁሞ በፅናት ታግሎ በማታገሉ እንጂ ጉዞው አልጋ በአልጋ አልነበረም::
በመጨረሻም ፋኖ ከሞቀና ከተደላደለ ቤቱ ለአማራ ሕዝብ የህልውና ተጋድሎ ወደ ትግል ሜዳ ከወጣ እለት ጀምሮ ለመስዋዕትነት ቆርጦና ተዘጋጅቶ እንደሆነው ሁሉ ሻለቃ ውባንተ ለአማራ ሕዝብ ነፃነት በክብርና በላቀ ጀግንነት ተሰውቷል:: ምንም እንኳ መስዋዕትነቱ ከባድ ቢሆንም ዐርበኛው የተነሳለትን ሕዝባዊ ዓላማ ለማሳካት በክቡር መስዋዕትነቱ ዳግም ቃላችንን በማደስ ለአማራ ሕዝብ ለማይቀር ድል ቆርጠን ተነስተናል::
በመሆኑም የአማራ ፋኖ በጎንደር ለመላው የአማራ ፋኖ፣ ለሕዝባችን እና ለትግላችን አጋሮች የሚከተሉትን ጥሪዎች ያስተላልፋል:-
1ኛ. የአማራ ፋኖ በጎንደር የጀግና መሪውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ በቀጣይ ቀናት “ዘመቻ ውባንተ” የተሰኘ በጠላት ላይ አዲስና በዓይነቱ ልዩ የሆነ የማጥቃት እርምጃ ይወስዳል:: ስለሆነም በቀጣይ የሚደረጉ የተጠኑ ስትራቴጂያዊ ዘመቻዎች በሙሉ “ዘመቻ ውባንተ” ተብለው እንዲጠሩ ተወስኗል::
2ኛ. መላው የአማራ ፋኖ በጎጃም፣ በወሎና፣ በሸዋ በተመሳሳይ ሁኔታ በቀጣይ የሚደረጉ የተጠኑ ስትራቴጂያዊ ዘመቻዎች እንዲወሰዱና ዘመቻዎችም በጀግናው መሪያችን በሻለቃ ውብአንተ አባተ ስም እንዲሰየሙ በኮር አመራር ደረጃ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ለዚህም ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እንዲጀመሩ ወታደራዊ ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡
3ኛ. ‹ዘመቻ ውባንተ› እንደአስፈላጊነቱ የፋኖ ኢንተለጀንስ መረጃዎችን መሰረት በማድረግ ከአማራ ክልል ውጭ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የአገዛዙ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ተቋማትና አመራሮች ላይ የማያዳግሙ እርምጃዎችን ለመወሰድ ስምሪት ይሰጣል፡፡
4ኛ. የመሪያችን ሻለቃ ውባንተ አባተ ሕዝባዊ የትግል ዓላማ እውን ይሆን ዘንድና ብዙ ርቀት የተጓዘው የፋኖ ትግል ፍፃሜ ያገኝ ዘንድ የዐርበኛው የትግል አደራ ለታጋዩ የአማራ ፋኖ በሙሉ ተላልፏል።
5ኛ. የመሪያችንን ሽኝት፣ ታሪክና በስሙ የተሰየመውን ዘመቻ አጠቃላይ አፈጻጸም በተመለከተ በቀጣይ ቀናት ተከታታይ መረጃዎችንና መመሪያዎችን የምንሰጥ ይሆናል::
በመጨረሻም ለሁሉም የፋኖ አባላት፣ ለአማራ ሕዝብና የትግሉ ደጋፊዎች እንዲሁም የቅርብ ጀግና ቤተሰቦቹ መፅናናትን እንመኛለን::
ሻለቃ ውባንተ አባተ እና ሌሎች ወንድሞች የሕይወት መሰዋዕትነት የከፈሉለት የአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል በድል እንደሚቋጭ እያረጋገጥን የሰማዕታት የትግል አደራ መቼውንም ቢሆን አይቀለበስም፡፡
ጀግና አይሞትም! የዐርበኛው ስም ከመቃብር በላይ ለዘለዓለም በክብር ሲወደስ፣ ሲዘከር መጠሪያ ሆኖ ይኖራል!
“ዘመቻ ውብአንተ”!
የአማራ ፋኖ በጎንደር
ጎንደር-ኢትዮጵያ
መጋቢት 10 ቀን 2016 ዓ.ም.