ፋኖነት ለሰብአዊ ክብር የሚከፍሉት ሰማዕትነት እንጂ የሚገዙትና የሚሸጡት የቅጥረኝነት አገልግሎት አይደለም!

ፋኖነት ለክብረ-ሰብእ፥ ለበዓለ-አገርነት፥ ለፍትሕና ለእውነት የሚሰጥ ክቡር ሕዝባዊ ሰማዕትነት መሆኑን ወዳጅም ጠላትም ይወቅልን

፳፬/፬/፳፻፲፮ ዓ/ም

የአገር ቤቱ ነባር ታሪክ፥ ሥነ ልቦና፥ እምነትና ትውፊት፥ ታሪክና የአገርና የሰብአዊነት ትርጉም የተለወጠብን እኛ የዘመኑ ምሁራን የፋኖን ትግል የምንረዳበት መንገድ፥ የምንደግፍበት ምክንያት፥ ተስፋ የምናደርገው ውጤት በጥንቃቄ መጤን ይኖርበታል።
ከአገራችን ነባር እሤቶች፥ እምነቶችና ረቂቅ የአገርና የሰውነት ትርጉም የራቅን ብዙዎች ነን። ሁላችንም አገራችንን እንወዳለን እንላለን። ይህ መውደድ በድምጽ ሲነገርና በጆሮ ሲሰማ አንድ ቢሆንም በልቦና ሲያድርና በተግባር ልንገልጠው ስንሞክር ተለያይቶ እናገኘዋለን።
ከ1960ዎቹ አብዮተኛ ትውልድ (በነባርነት ላይ ያመፀ ትውልድ) ዘመን ወዲህ በቃላትና በመዝገበ ቃላት አንድ ብንሆንም በልብ፥ በርእይ፥ በአገርና በሰው ትርጉም ላይ አያሌ ልዩነት ፈጥረናል። በዚህ ልዩነት ምክንያት የአማራን ሕዝብ የህልውና ተጋድሎ በተግባር ራሱን ከሚገልጠው በተለየ መንገድ ቅርብን ሆነ ሩቅ ያሉ ተመልካቾች የተለያዩ ግምቶችና መረዳቶችን ይዘው መቸገራቸውን እየተመለከትን ነው። በተለይ በከተማና በውጭ ሆነን ትግሉን በቀናነት ለመደገፍ የምንሞክር፥ እንዲሁም በሕዝቡ ላይ የሚደርሰውን ሁለገብና የማያባራ ሥርዓታዊ ጥቃት በመመልከት በኅሊና አስገዳጅነት ወደ ትግሉ ሜዳ የገባን ወገኖች ራሳችንን በጥንቃቁ በመርመር እኛ ሕይወታችንን ለሕዝባችን ያቅርብን ወንድም አኅቶቻችሁ ከሰነቅነው የህልውና ዓላማና አገራዊ ግብ፥ ከአካሄዳችንና ከምንገኝበት ሁኔታ ጋር የሚቀራረብ መረዳት እንዲኖረን መጣር ይገባል።
ከሕዝቡ መካከል መከራ አስፈንጥሮት የፋነነው የአማራ ፋኖ፣ ከሩቅ መከራውን ለመካፈል ተወርውሮ ከሚፋንነው ጋር ብዙ የሚጋሩት እሤት ቢኖሩትም ምኞታቸውና ርእያቸው የተወሰነ ልዩነት ሊኖረው ይችላል። ከውስጥ የተስፈነጠረው የመጀመሪያ ትኩረቱ የወገኑ ህልውና ነው፥ ሁለተኛው ህልውናውን ዘላቂና ዋስትና ያለው የሚያደርገውን ሥርዓተ መንግሥት ማቆም ነው። በሌላ በኩል ከውጭና ከሩቅ ተስቦ የመጣው ሁለቱንም ግብ የሚጋራ ሆኖ አንድ ሌላ ተጨማሪ የልብ ውስጥ አጀንዳ ይሸከማል። እነዚህ ሸክሞች ትግሉ ሲጠናቀቅ የሚያገኘው የፖለቲካ ሥልጣን፥ የሕዝብ ክብርና ዝና ሊሆን ይችላል። እነዚህ ተጨማሪ ሸክሞች በራሳቸው ትግሉን የሚጎዱት ባይሆኑም ከሚፈለገው በላይ ከተተኮረባቸው ትግሉን የሚያኮላሹ አደገኛ መርዞች ናቸው።
የአማራ ባህላዊና ነባር ፋኖነት መሠረቱ የሕዝቡ እምነት፥ ባህል፥ ረዥም ታሪካዊ አገርን እና የሰው ልጅን ክብር የማስጠበቅ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ትግል ቃልኪዳን ነው። ይህ ቃል ኪዳን ግለኝነትን የሚጸየፍ ትውልዳዊና አገራዊ ግብ ያለው በመሆኑ ግለኝነት የተጫናቸው ብልጦች፥ ቁማርተኞችና ራሳቸውን ከሰማዕትነት በማሸሽ ለሥልጣን የሚያደቡ መሪዎችና፥ “አይተነው ጊዜው ወደሚያደላ” የሚሉ አድርባዮችና ባንዶች ጠላቱ ናቸው።
ፋኖ ዓለም አቀፍ ዳሰሳ፥ የጂኦ ፖለቲካ አሰላለፍ፥ የመሣሪያ በቂነት ትንተና እና ልዩ የተመረጠ ሥልጡን መሪና ቀስቃሽ፥ ገንዘብና የግል ተስፋ የሚያንቀሳቅሰው ኃይል አይደለም። ፋኖነት አሁን ከዘላለማዊነት፥ ሥጋን ከመንፈሳዊነት፥ ዛሬን ከመጭው ትውልድ፥ ሠፈርን ከአገር፥ የግለሰብን ክብር ከሕዝብ ክብር አቆራኝቶ በሰብአዊነት፥ በፍትሕና በእውነት አምዶች የሚመራ መሪ የማይሞትበት፥ መሪ የማይነጥፍበት፥ መሸጥና መግዛት የማይስማማው ንቅናቄ ነው።
በዚህ ምክንያት ፋኖ የቅርብና የሩቅ ሶስተኛ ወገን ፈቃድ፥ ስጦታ፥ የሞራልና የፖለቲካ ድጋፍ መኖርና አለመኖር የሚለዋውጠው እሥረኛ ኃይል ሳይሆን ግፍን በማንኛውም ዋጋ፥ ሁኔታና ጊዜ በሰማዕትነት ለማሸነፍና በሰውነት ለመገኘት የሚወለድ ንቅናቄ ነው።
ከዘረኞቹ የፋሽስት የፖለቲካ ሥርዓቶችና መንግሥታዊ ተቋማት ጋር ግብግብ ውስጥ የገባው ፋኖ የፖለቲካ ሥልጣን፥ ገንዘብና ትጥቅ አሰናድቶ፥ መልምሎ፥ ኢንዶክትሪኔሽን ሰጥቶ አሰልጥኖና፣ አስታጥቆ በዲሲፕሊንና በድርጅታዊ አሰራር ተጠርንፎ የዘመተ እና ትዕዛዝ የሚጠባበቅ ቅልብ ጦር አይደለም።
ፋኖ የመኖር ተፈጥሮአዊ ግዴታ፥ ትውልድና አገርን የማስቀጠል ከደመነፍሳዊነት ከፍ ያለ ታሪካዊ፥ መንፈሳዊ፥ ሰብአዊ እና ሕዝባዊ ቃልኪዳን የሚመራው እሳተ ገሞራ ነው። ይህ እሳት የሚቀዘቅዘው ሰብአዊነትን ከሐሰተኞች፥ ከቁማርተኞች፥ ከተንኮለኞች፥ ከአልጠግብ ባዮችና ከዘርና አገር አጥፊ ድዉያነ ኅሊና የዘር ፖለቲከኞች የመታደግ ግብ መሳካት ብቻ ነው። ይህን እሳት ነበልባሉና ግለቱን መመጠን እንጂ ማጥፋት አይቻልም። የውጭ አመራር ሆኖ እርዳታና ምክር የሚሰጥ ሰው፣ ትግሉን የሚለኩሰው፥ የሚያራግበው ወይንም በተቃራኒው የሚያጠፋው ባለመሆኑ ድጋፍ ለመስጠት የሚፈልግ ሁሉ ድጋፉን በፍቅርና በፋኖ ዓላማ በመገዛት እንጂ ፋኖን ለመግዛትና ለመምራት ከሆነ እሳቱ የተገዥነት ተቃራኒ ስለሆነ ወደ ውስጥም ያቃጥላል።
ይህንን ንቅናቄ ወራሪዎች ያሳደጓቸው የባንዳ እና የቅኝ ገዥዎች እምነትና ፍልስፍና ሰለባ የሆኑ የሐሰት ትርክት ቅዠትን ሳይንሳዊ ለማስመሰል በደረቱት የሕትመት ብዛት ምሁር እና ልሂቃን የተሰኙ አይረዱትም።
ይህን ንቅናቄ ከአድዋው ሽንፈታቸው ማግሥት ጀምሮ ፋኖነት ድንቅ ኢትዮጵያዊ ሰብእና መሆኑን በመረዳት ለዚህ ሰብእና መሠረት የሆነቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን፥ ነባር ኢትዮጵያዊ እስልምናን እና ነባር ባህሎችን በማይታወቅ አዲስነት ለመተካት ለብዙ ዘመናት የሠሩ የውጭ አማካሪዎችና ምሁራን የሚደግፏቸው ናቸው።
ፋኖን መደገፍ የሚሻ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በትንሹ መገንዘብ የሚገባው ላለፉት 50 ዓመታት በሥልጣን ላይና በፖለቲካ ቁንጮ ላይ የተፈናጠጡት ቡድኖች ሰብአዊነትን ደፍቀው የየጎሣቸውን የቡድን መንጋ በመፍጠር ነገሥታት ለመሆን የሚሹ የሥልጣን ጥመኞች፥ ኅሊና ጎድሎአቸው ሆድ የነገሠባቸው የዘመናችን ፖለቲከኞች ከፋኖነት እሴትና ሰብእና ጋር ፍጹም ተቃራኒ ናቸው።
የሚያሳዝነው ለዚህ መልእክት መጻፍ ምክንያት የሆነው ፋኖን እንደግፈዋለን ብለው ከልባቸው የሚደክሙ ነገር ግን የውጭ ጠላት የተረዳውን የፋኖነት ሥነ ልቡና መረዳት ተስኗቸው በሚሰጡት ድጋፍና እርዳታ ሊገዙትና ሊሸጡት፥ ሊጠመዝዙትና ሊሸቅጡት፥ ሊከፋፍሉትና መሣሪያ ሊያደርጉት የሚመኙ መልካሞች ነገር ግን አላዋቂ ግለሰቦች ጉዳይ ነው።
ፋኖ ሁሉም እንደሚያውቀው በራሱ ጠመንጃ፣ በራሱ ቀለብ፣ በራሱ ልብስ፣ በራሱ ህይወት ትግል ውስጥ የገባና እስካሁንም ያስመዘገበው ድል በሌሎች ሶስተኛ ወገኖች ድጋፍ የተገኘ ሳይሆን በራሱ ሀብትና ቁርጠኝነት ነው። የአገር ውስጥና የውጭ ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ድጋፍ ጥቅሙ ከፍ ያለ ቢሆንም ወሳኝና የፋኖን መሠረታዊ ማንነት የሚቀይር አይደለም። ምክንያቱም ዋናው በገንዘብ ሊገኝ የማይችለው የዘመናት ፋኖአዊ እሴትና የወገንና የአገር ህልውናን የሚደግፍ ሰብአዊና ትውልዳዊ እሴት በዲያስፖራ ድጋፍ የተገኘ ሳይሆን በራስ ሀብትና ቁርጠኝነት የተገኘ ነው።
ፋኖ ለሀገሩና ለወገን ፍቅር ብሎ ህይወቱን ለመስጠት የወጣ እንጂ አንዱን ለማንገሥ ሌላውን ለማቀሰስ የወጣ ኃይል ወይንም በምናባቸው ራሳቸውን በራሳቸው አንግሠው አጋጣሚዋን ለመጠቀም አድፍጠው የሚጠባበቁትን ለመጠበቅ የተመሠረተ የክቡር ዘበኛ አይደለም። በትግሉ ውስጥ ገብቶ፣ ታግሎ የሰውን ልብ ገዝቶ የሚነግሥ፥ ገዳም በረሓ ወድቆ ከአጋንንት ተዋግቶ፥ ቅድስናን ከእግዚአብሔር አግኝቶ በገቢረ ተዓምራት አምላኩ የገለጠው፥ ምእመናን ይሾምልን ብለው በገመድ አሥረው ግድ ያሉት የሚቀስስ ግን አይኖርም ለማለት አይደለም። በትግል ውስጥ ታጋይም መሪም ይወለዳልና።
ፋኖ የፈቃደኛ ጦር ስለሆነ ልቡ ከሻከረ ስሜቱ ከተጎዳ በትግሉ አላማና ግብ ጥርጣሬ ካደረበት ጠመንጃውን ይዞ ወደ ቤቱ ከመመለስ የሚያቆመው ኃይል የለም።
ፋኖ የተያዘው በሀገርና በወገን ፍቅር እንጂ በዲሲፕሊን፣ በድርጅታዊ ጥርነፋ ወይም በደሞዝ አይደለም።
የፋኖ ፈቃደኛ (volunteers) ታጋይ ስለ ትውልድና እውነት፥ ስለ ፍትህና ሰብአዊ ህልውና ሊሰዉ የቆረጡ ሰዎች የፈጠሩት እንጂ ሥልጣንና የሳንቲም ድቃቂ፥ የዘረፋ ግዳይ እጣ ተመኝተው በየጥሻው ሰው እንደሚያርዱት የኦነግ ሠራዊትና የሕወሐት ሳምሪ ቡድን በግፍ ከፍ ለማለት የተሰባሰበ የአጭር ጊዜ ፍትወቱን ለማርካት የነሆለለ የወንጀለኞች ቡድን አይደለም።
ስለዚህ እንደግፈዋለን የምንል፥ ልምራህ ብለን ትግሉ ሳይወልደን ራሳችንን ከሾምን፥ የልቡን ያልተረዳን ሲመስለው፣ ስሜቱን የሚጎዳ ነገር ሲደረግ ካየ፣ እየከፋፈልነው ከመሰለው፣ ያታለልነው ከመሰለው፣ እየተጠቀምንበት ከመሰለው ወይንም ከሀገር ጥቅምና ነጻነት በላይ ለራስ ስልጣንና ጥቅም በህይወቱ እየነገድን እያተረፍን ከመሰለው በማንኛውም ሰዓት ጠመንጃውን ወደ መሪዎቹ አዙሮ ረሽኖ ወደ ቤቱ ከመመለስ የሚያስቆመው ምንም አይነት ኃይል የለም። ይህን ለማድረግ የምንሞክር ሁሉ የብአዴን እጣ ፈንታ ከኛም ሩቅ አይደለም።
ፋኖ ሀገር ነጻ አወጣለሁ ብሎ “የበላው ቀብድም የለም”። ስለዚህ ቤቱን ጥሎ በፈቃዱ እንደ ወጣ ሁሉ፣ ልቡ የሻከረ ወይንም የተጠቀምንበት የመሰለው ቀን፣ አለ ብለን ስንኮፈስ የት ገባ የሚባል ኃይል ሊሆን ይችላል።
ፋኖን እንደሚገባ ሳንረዳው፥ ወይንም አብረን በመከራው ሳንሳተፍ ለድጋፍ የተሰባሰብን የዛሬዎቹ እኛ፣ የቀድሞዎቹ ኮሚኒስቶችም ስለ ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያውያን መረዳት ተስኗቸው አገራቸውን ለዛሬ የሚተርፍ መቀመቅ ውስጥ ጨምረዋት ለአማራ ሕዝብ የዘር አጥፊዎች ፕሮጄክት አመቻችተው ራሳቸውን እንዳጠፉት ሁሉ፣ እኛም ለሁላችንም ነፃነት የተነሳውን ፈቃደኛ ወጣትና ሕዝብ በሌኒኒስት ድርጅታዊ ጥርነፋ አምሳል ልናሰነካክለው ከመሞከር መታቀብ ይኖርብናል። ይህ ተዋጊ በፍቅር እንደመጣ በጥርጣሬ ጥሎ ሊሄድ ይችላል። ከዛም አልፎ መሪዎቹን ሊበቀል ይችላል።
ይህንን እንዳያደርግ የሚከለክለው ምንም ገመድ የለም። ስለዚህ የፈቃደኛ ጦርን መምራት እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ወታደራዊ ክንፍ ቀላል አይደለም። እንደ ህወሓትና እንደ ሻዕቢያ ጦር አይደለም። ከፍቅር በቀር ምንም ያሰረው ክር የለም። ለዚህ ነው ትልቅ ጥንቃቄና ትልቅ የሥነ ልቦና ብልጽግና (Emotional Intelligence) ያለው አመራር የሚያስፈልገው።
ፋኖን በመርዳት ስም በትግል ውስጥ የተፈጠሩትን መሪዎች እኛ እንምራችሁ የምትሉ የሩቅና የቅርብ ብልጣብልጦች ይህን ለሰማዕትነት መዘጋጀቱን በተግባር እያስመሰከረ የሚገኝ ሕዝብ መርታችሁ ለድል ላታበቁት “ይህን የምረዳህ ለእገሌ ተጠሪ ስትሆን ነው” የሚለውን መልእክት በማስተላለፍ ታጋዮቹን ባታስቆጡና አንድነቱ ላይ ጫና ባታደርጉ መልካም ይሆናል። ይህ ባይሆን ግን ውጤቱ የከፋና ብዙዎችን የሚጎዳ፥ ከፋኖነት እሤትና መርህ ውጭ ንግዳዊና ድርጅታዊ ጠባይ ይዞ ህልውናውን ከአደጋ ለመታደግ በተነሳው ሕዝብ ላይ ወንጀልም ኃጢአትም ትሠራላችሁ።
በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ተለምኖና በተፈጥሮአዊ የህልውና ማስጠበቅ ግፊት ለመስዋዕትነት የመጣን ኃይል በጨቅላ አስተሳሰብ መከፋፈል ትልቅ ጸረ ኢትዮጵያዊነት ነው።
ያለፈው ትውልድ በእንጭጭ አስተሳሰብና ችኩል ብያኔዎቹ ንጉሡን በማነቅ ጳጳሱን በመግደል ኦርቶዶክስን በማጥፋት አማራውን ከእርስቱ በማፈናቀል ኢትዮጵያን እንጠቅማለን ብለው እንደሞከሩት እና አገርም፥ ክብርም፥ ታሪክም፥ ማኅበራዊ ትሥሥርም፥ ቁሳዊ ልማትም በማጣት በዛሬው አራጅ አሳራጅ ፖለቲካ ሥር እንደወደቀው ሁሉ፣ ጨቅላነት ድልን አያጎናጽፍም።
አሁን ትልቅ ችግር እየተጋረጠ ነው። በርካታ ታጋዮች ሚስታቸውን፣ ልጆቻቸውን፣ ስራቸውን፣ እርሻቸውን፣ ንግዳቸውን፣ አሮጊት እናታቸውን፣ እቁባቸውን ጥለው የወጡት የወገናቸው መጠቃት እና በፋኖ ውስጥ የተፈጠረው ወንድማማችነት ስሜትና ትብብር ነው።
ይህንን የሥነ ልቦና ትስስር (psychological contract) የሚሸረሽር ነገር ከተሰራ ሁሉም ነገር እንደ እምቧይ ካብ ይበተናል ባይባልም የህልውና ትግል ተፈጥሮአዊ ስለሆነ ሕዝባዊ፥ ነገር ግን አዝጋሚና የተበታተነ ሆኖ ይቀጥላል። የተጀመረው በመዋቅር ደረጃ ያልተማከለው፥ በግብና በርእዮት ፍጹም አንድ የሆነውና ባለፉት 2 ዓመታት ውስጥ ለውስጥ የተዘጋጀው መሥመር በድንገቴ መሪዎች የሚበላሽ ከሆነ መስዋዕትነቱን ከፍተኛ ያደርጋል።
ስለዚህ
፩) ሁሉም ፋኖ አንዲት ህይወቱን ለመስጠት የተዘጋጀ ነውና የሚበላለጥ የፋኖ ነፍስ እንደሌለና መከራውንም ይሁን ድጋፉን እኩል ማግኘት ስላለበት በግድ አንድ ካልሆንክና ለእገሌ ተጠሪ ካልሆንክ ድጋፍ አታገኝም የሚል ምልክት በመሬት ላይ እየተመለከትን ይህን እኩይ ዝንባሌ በዝምታ ማለፍ አይገባንም። ይህን የሚያደርግ ቡድንና ግለሰብ ሁሉ የአማራን ህዝብ ደም የሚያራክስ፥ ባርነቱን የሚያስቀጥልና ከባንዳዎች የከፋ ሆኖ በታሪክ ይዘከራል።
፪) ከየትኛውም ኢትዮጵያዊ የሚሰጥ ድጋፍ ለሁሉም ፋኖና ለትግሉ እንጂ ለተወሰኑ ሚዲያዎች ወይንም ብልጠት የሚያነግሣቸው ግለሰቦችን የስልጣን ፍላጎት ማሟያ የተሰጠ በጀት እንዳልሆነ በመረዳት ድጋፍ አሰባሳቢዎች ሁሉ በአደባባይ ወጥታችሁ በድጋፍ ስም የሚደረገውን አድልዎና ከፋፋይነት ማውገዝ ይኖርባችኋል፡፡
፫) በፋኖ ድጋፍ ስም የተሰበሰበ ማንኛውም ሀብት እስከተቻለ ድረስ ለሁሉም ፋኖ እና ህይወታቸውን ሊሰጡ ለተዘጋጁ እንደሚደርስ የሚታወቅ እንጂ የሕዝብ የህልውና ፈተና ያጣመራቸውን ፋኖዎች በብርና በጥቅም በመግዛት ለግል ጥቅም ለማዋል እንዳልሆነ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም እንዲህ ሊያደርግ የሚሞክር ሁሉ የተወገዘና የአማራ ሕዝብ ጠላት መሆኑን በአደባባይ መግለጥ ይገባል።
፬) ከሰው ይልቅ ገንዘብን አክብሮ፥ ለሰማዕትነት የቀረበን የሰው ልጅ በማቅለል በገንዘብ ለመግዛት መሞከር ዋጋ ያስከፍላል፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ታጋዮች ይህን ያደረገ ማንኛውንም ወገን የህልውናው ጠላት መሆኑን አውቀው እንደሚቀጡት በመረዳት ሕይወት የሚከፈልበትን ትግል ተሽከርካሪ ወንበር ላይ እንዳለ የከተማ ፖለቲካ፥ ወይንም እንደ ማርክሲስቶቹ አብዮተኞች የሤራ ፖለቲካ ወደ ቁማር ዝቅ ማድረግ ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት ስለሚሆን በዚህ የምትሳተፉ ወገኖቻችን ሁሉ በአደባባይ እንደምታወግዙት ይጠበቃል።
፭) አንዳንድ ብዙ ተከታይ ያላቸው ሚዲያዎችና ግለሰቦች በመሬት ላይ የሚካሄደውን፥ የአደረጃጀትና የመሪዎቹን ታሪክ በሚገባ ሳያጠኑ ለስሜታቸው መልካም መስሎ የታያቸውን ወሬ በማጠረቃቀም አንዱን የማንገሥና ሌላውን የማጠልሸት ሚና ውስጥ መግባታቸው የአማራን ሕዝብ የህልውና ትግል ከመጉዳቱም በላይ መሪዎቹንና ሁኔታዎቹን የሚረዱ ታጋዮች ትዝብት ውስጥ በመውደቅ መተማመንን አዳክሞታልና ይህ ቢገታ መልካም ይሆናል።
፮) የኢትዮጵያ ትግል ለ50 ዓመታት ድል ያላመጣው ገና ድል የታየ ቀን እርስ በእርስ መጠፋፋት ስለሚጀመር ነው፤ ዛሬም በጠላት እጅ ላይ ወድቀው በእሥር ቤት የሚንገላቱ ታጋዮቻችንን ስም ማጥፋትና መከፋፈል ለሕዝባዊ ትግሉ የሚሰጠው ፋይዳ ምን እንደሆነ በማንረዳበት ደረጃ ሥራዬ ብሎ የመከፋፈልና የመፈረጅ ሥራን መሥራት የትግሉ ጠላት ከመሆን የማያልፍ በመሆኑ ቢቆም መልካም ይሆናል።
፯) በአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል ውስጥ ራሱን ለሞት አሳልፎ በመስጠት እየደማ የሚገኘውን ፋኖን ለመምራት በእቅድና በውይይት መሪ ልሁን ብሎ የሚነሳ ሁሉ ይወድቃል፥ የፋኖ ታሪክ የሚያሳየው መሪዎች በትግሉ ውስጥ ይወለዳሉ፥ ያድጋሉ፤ አንመራም ብለው እምቢታ ቢያሳዩ እንኳን መርቶ ለድል ያበቃቸውን የሚያውቁ ታጋዮች የግድ ይሉታል፤ ከዚህ የተቃረነ፣ በግለኝነት (ኢጎ) የሚነዳ መሪ የመሆንና የመፍጠር ሩጫ ትግሉን ከመጉዳት የበለጠ የሥልጣን ፈላጊዎችን ከፍተኛ አደጋ ላይ ይጥላቸዋል፥ ፋኖአዊ ባህልና መርህን በዘመናዊ ሤረኝነት ያቆሽሸዋልና ይቁም።
በመጨረሻም የህልውና ትግሉን በወንድማማችነትና በሀገር ፍቅር እንጂ በብር ለመግዛት መሞከር ታላቅ ውድቀትን ያስከትላል፤ አንድም ፋኖ ከትግሉ አዝኖ ከወጣ አንድ ሺ ሰው ትግሉን ጥሎ እንደወጣ ስለሚቆጠርና ስንጥቃት ስለሚፈጥር በድጋፍ ስም ምንም አይነት ጫና ማሳየት በትግሉ ላይ በጠላትነት እንደመነሳት ስለሚቆጠር ደጋፊዎች ከፋፋይ እርዳታዎችን እንድታግዱ እናሳስባለን።

የሸዋ፥ የጎንደር፥ የወሎ፥ የጎጃም ፋኖዎች የአንድነት ምክር ቤት አባላት መሪዎች
ልንሰዋለት ከቤታችን የወጣንለት ሕዝብ አምላክ አንድነታችንን ይጠብቅልን

13 thoughts on “ፋኖነት ለሰብአዊ ክብር የሚከፍሉት ሰማዕትነት እንጂ የሚገዙትና የሚሸጡት የቅጥረኝነት አገልግሎት አይደለም!

  1. ከ60ዎቹ ትውልድ በተጨማሪ ከ1970ዎቹ መጨረሻ በቡድን ነጻ አውጭነት ራሳቸውን ሰይመው ሕዝብን በአእምሮአቸው ልኬታ ግብና ርእይ ሰፍተዉለት አእምሮ እንደሌላው መንጋ እያስከተሉ ያፋጁ ልሂቃን ዛሬም የፋኖን የህልውና ትግል ሳይቀር ጠልፈው የሥልጣን ጥማቸው አቋራጭ ማርኪያ የማድረግ ምልክት እመለከታለሁ። አንዳንዶች በፋኖ ስም ከዲያፖራ የለመኑትነ ገንዘብ ይዘው ለእገሌ ካልገበርክና እንደ አለቃህ ካልተቀበልክ ገንዘብ አታገኝ በሚል ዕለት ዕለት ስልክ እየደወሉ ፋኖዎችን ሲያውኩ ይታያሉ። አንዳንዶች በሚዲያው ዘርፍ ትግሉን የሚደግፉ ሳይቀሩ ለእገሌ ካልተገዛህ ዜናችሁን አንዘግብም ሲሉ ሰምተናል። ይህ ጽሁፍ ለእነዚህ አይነት ደካሞች ዓይን ገላጭ የሚሆን ይመስለኛል። እናመሰግናለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *